November 23, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሴቶች በልማት ሥራዎች ንቁ ተሳታፊና የሀብት ባለቤት እንዲሆኑ ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጥሪ ቀረበ።

የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሴቶች በልማት ሥራዎች ንቁ ተሳታፊና የሀብት ባለቤት እንዲሆኑ ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጥሪ ቀረበ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አዲስ በተሻሻለው የሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀት አሰራር መመሪያ ዙሪያ ከሸካ ዞንና ከቴፒ ከተማ ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ስልጠና ሰጥቷል።

ስልጠናውን የሰጡት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሪት ለምለም አምሳሉ በኢፌደሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 35 መሠረት የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታስቦ የቀድሞ የሴቶች ልማት ቡድን የነበረው አደረጃጀት ተሻሽሎ የሴቶች ልማት ህብረት በሚል ማደራጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል።

ስልጠናው ሴቶች በተለያዩ የልማት ሥራዎች ተሰማርተው የገቢ ባለቤት ከመሆንም ባሻገር ሀብት እንዲያፈሩ ያለመ ነው ብለዋል ።

አክለውም ህብረቱ የጋራ ዓላማና ግብ ያላቸው በተመሳሳይ አካባቢ ያሉና ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑትን ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ የሆኑትን ሴቶች የሚያካትት የ1 ለ 10 ትስስር ነው ብለዋል።

ከልማት ሥራም ባሻገር ሴቶች ለሠላም ዘብ በመቆም ፣ የራሳቸውንና የልጆቻቸውን ጤና እንዲጠብቁና በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዝ አደረጃጀት መሆኑን ተናግረዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው በቂ ዕውቀት ያስጨበጣቸው በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀው በዚህም በቀጣይ ሰርተው ለመለወጥ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከዞንና ከከተማው መዋቅር በስልጠና መድረኩ የተገኙት አመራሮች በበኩላቸው የሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀትን በማጠናከር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በጋራ ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

መድረኩን በጋራ የመሩት የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሪት ለምለም አምሳሉ ፣የሸካ ዞን ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት ከበደና የቴፒ ከተማ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ወይዘሮ ታሪኳ ይርሲ ስልጠናውን በቀጣይ ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባና በተለይ ሴቶች ተደጋግፈው መሥራት እንዳለባቸው መልዕከት አስተላፈዋል ።

በስልጠናው ላይ ከሸካ ዞንና ከቴፒ ከተማ የተውጣጡ ስትሪንግ ኮሚቴዎች፣ ባለሙያዎች፣ የሴቶች ልማት ህብረት መሪዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ጌትነት ገረመው

You may have missed