የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የ’ገበታ ለሀገር’ ፕሮጀክቶችን ለየክልሉ አስረከበ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለተከናወኑት የ’ገበታ ለሀገር’ ፕሮጀክቶች ዛሬ አንድ ሌላ ምዕራፍ ተከናውኗል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዛሬ ባዘጋጀው መርሃ ግብር ፕሮጀክቶቹን ለአማራ፣ ለኦሮሚያ እና ለደቡብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስረክቧል።
በተጨማሪም በገበታ ለሀገር የተገነቡ ሎጆችን ስራ የማስኬድ ተግባርን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በስካይ ላይት ሆቴል ተቋሙ በኩል እንዲወጣ የስምምነት ፊርማ ሥነሥርዓት ተካሂዷል።
ከአራቱ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ሶስቱ (ሃላላ ኬላ ሎጅ፣ ጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ እና ወንጪ ኢኮ ሎጅ) በቅርቡ መመረቃቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የጎርጎራ ፕሮጀክት ስራም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
በጠቅላይ ሚኒስሩ ከፍተኛ ትኩረት እና አመራር የተከናወነው የ’ገበታ ለሀገር’ ስራ የብሔራዊው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ ማዕዘን የሆነውን ቱሪዝምን የማሳደግ ዓላማ ያለው ነው።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በመጀመሪያው ፋይናንስ የማሰባሰብ ምዕራፍ የኅብረተሰቡን ድጋፍ በሰፊው ያሰባሰቡ፣ በግንባታቸው ምዕራፍ ግዙፍ የስራ ዕድል የፈጠሩ ብሎም ታላላቅ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲከናወኑ በር የከፈቱ ናቸው።
በፈጠራ የተሞላ የፕሮጀክት ስራ እና አስተዳደር እና ፈጣን አፈፃፀም ምን ሊመስል እንደሚችል ማሳያም ሆነዋል።
ቀጣይ የስራ ማስኬድ እና ማስተዳደር ተግባሩ ለብሔራዊ ሰንደቅ ተሸካሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሃላፊነት መሰጠቱም የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ከማስቻሉም ባለፈ ለዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻነት ትውውቅ ከፍ ያለ ዕድል እንደሚፈጥር ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
More Stories
አቶ ሽመልስ አብዲሳ የ ‘ሆረ ፊንፊኔ’ ኢሬቻ በዓል በድምቀት እንዲከበር ያደረጉ አካላትን አመሰገኑ
የጎንጋ ህዝቦች የልማት፥ የወንድማማችነትና የአብሮነት ፎረም እየተካሄደ ነው።
የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊያን የአንድነትና የመከባበር ኃይል የሚያሳይ ትልቅ መሰባሰቢያ መድረክ ነው ሲሉ የበዓሉ ታዳሚዎች ገለጹ።