April 28, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሙስናን ለመከላከል በተደረገው ጥረት ከ85 ሚሊዮን በላይ ብር የህዝብ ሃብት ማዳን ተችላል

ማሻ ፣ የሚያዝያ 19፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሙስናን ለመከላከል በተደረገው ጥረት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥትና የህዝብ ሃብት ከምዝበራ ማዳን መቻሉ ተገለጸ።

የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ ለኢዜአ እንዳሉት፥ ኮሚሽኑ ሙስናን የመከላከል ተግባር ላይ የህብረተሰቡን ድርሻ ለማሳደግ ግንዛቤን የማስፋት ስራ ተጠናክሮ እየተሰራ ነው።

የሙስና ወንጀልን ቀድሞ በመከላከልና ተፈፅሞ ሲገኝም ማስረጃ በመተንተን ለፍትህ አካላት የማቅረብ ስራ በትኩረት መሰራቱን ገልጸዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ባለፉት 9 ወራት ኮሚሽኑ በተለያዩ ዘዴዎች ከተቀበላቸው 475 የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች ውስጥ 399 ጉዳዮችን በማጣራት ውሳኔዎች እንደተላለፈባቸው እና ቀሪዎቹ በሂደት ላይ እንዳሉ ተናግረዋል።

በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ስራ ከ39 ሚሊዮን 822 ሺህ ብር በላይ ማዳን የተቻለ ሲሆን በአሰራር ጥሰት ባክኖ የነበረ ከ45 ሚሊዮን 267 ሺህ ብር በላይ በኦዲት ግኝት እንዲመለስ መደረጉን ኮሚሽነር ሙሉሰው ጠቁመዋል።

ከገንዘብ በተጨማሪ ከ15 ሺህ 183 ካሬ በላይ የከተማ መሬት እና 353 ሄክታር የገጠር መሬት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ንብረቶችን ማዳንና ማስመለስ ተችሏል ብለዋል።

ሙስናን መከላከል የሚያስችሉ ችግር ፈቺ ጥናቶችን ማካሄድ፣ የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ እንዲሁም ትክክለኛነቱን የማጣራት ስራም ኮሚሽኑ ትኩረት የሰጠው ሌላኛው ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።

በተሰራው ስራም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የ3 ሺህ 54 አዳዲስ የመንግስት ሰራተኞችን ሀብት የማስመዝገበ እና የምስክር ወረቀት የመስጠት ስራ መሠራቱንም ኮሚሽነር ሙሉሰው አንስተዋል።

ከሚሽኑ ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ጥቆማዎችን እንዲያጠናክርም ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።