April 28, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ኢትዮጵያ እና ኢንግሊዝ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ እና ኢኮኖሚ ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ ተስማሙ

ማሻ ፣ የሚያዝያ 19፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) ኢትዮጵያ እና ኢንግሊዝ ከልማት ድጋፍ ባለፈ የሁለቱን ሀገራት የኢንቨስትመንት፣ የንግድ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር በማሳደግ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸው ተገለጸ።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከእንግሊዝ የዓለም አቀፍ ልማት ሚኒስትር ባሮነስ ቻፕማን ጋር ከ2025 የአይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ የፀደይ ስብሰባ ጎን ተወያይተዋል።

ሚኒስትሮቹ በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ አጋርነት እንዲሁም የጋራ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጥቅሞች ላይ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችል ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ ስኬታማነት አስመልክቶ ለሚኒስትሯ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን፤ የሪፎርሙን ቀጣይነት ያለው ስኬት ለማረጋገጥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን የሚደግፉ የልማት ስራዎችን ለማጠናከር ቀጣይነት ያለው የሁለትዮሽ ሥራ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ልማት ሚኒስትር ባሮነስ ቻፕማን በበኩላቸው የኢኮኖሚ ሁኔታውን ለማሻሻል የተደረገውን ሪፎርም አድንቀው፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ መረጋጋት ላይ ቀጣይነት ያለው አስተዋፅዖ እንድታደርግ ጠይቀዋል።

እንግሊዝ ኢትዮጵያ ያላትን ትልቅ አቅም በመጠቀም እድገቷን እንድታስቀጥል የሚያስችላትን እገዛ ማድረጓን እንደምታጠናክርም አረጋግጠዋል።

ፋና