April 3, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የመረጃ ተደራሽነት በማስፈን ጥራት ያለውን መረጃ ለአድማጮች ለማድረስ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተገለፀ ።

ማሻ ፣ የመጋቢት 18፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የሸካ ማህበረሰብ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ያለበት የስራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ከመጡት ባለድርሻ አካላት ጋር በማሻ ከተማ ውይይት ተደርጓል ።

በውይይቱ ላይ የሸካ ማህበረሰብ ራዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ እስከአሁን ስላከናወናቸው ተግባራትና ቀጣይ ውጤታማ ስራ መስራት በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳብና አስተያየት ተሰጥቷል ።

በውይይት መድረኩ ላይ የሸካ ማህበረሰብ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና አዘጋጅ ተወካይ አቶ ታደሰ ጋረፎ ባቀረቡት የስራ ሪፖርት ጣቢያው ከደቡብ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊ ግብዓቶችን በሟሟላት ውጤታማ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

ያለውን ሀብት አደራጅተው ከመጠቀም አንፃር የአሰራር ስርዓት በመከተል የሸካ ማህበረሰብ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ቦርድ ተቋቁመው ወደስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ባስቀመጠው የስራ አቅጣጫ አምስት የቋሚ ሰራተኞች ጋር በመሆን በበጎ ፍቃድ ከሚሰሩት 43 ሰራተኞች ጋር በርካታ ስራዎች እየተሰራ እንደሚገኝ ለባለስልጣኑ ጠቁመዋል ።

ተቋሙ በትምህርት ፣በጤና እንዲሁም በግብርናና ሌሎች ዘርፎች ላይ በሸኪኖኖ፣በአቶ ማጃንግና አማርኛ ቋንቋዎች መረጃዎችን ለአድማጮች የማድረስ ስራ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

ከዚህ የበለጠ ተግባራትን ማከናወን እንዳይችል የሰው ሀይል በስልጠና የመገንባት ችግር፣የስርጭት ተደራሽ ያለመሆን፣የተለያዩ የሚዲያ ግብዓቶች እጥረት መኖር እንዲሁም በዋናነት የትራንስሚተር ፣ ሰርቨር እና የሎጂስቲክ እጥረት መኖር ተግዳሮቶች መሆናቸውን ገልፀዋል ።

የሸካ ማህበረሰብ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የቦርድ አባል ወ/ሮ ትዕግስት ጌታቸው በበኩላቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች ለመገምገም በመምጣቱ ምስጋናቸውን አቅርበው ይህ አይነት ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።

ለሸካ ማህበረሰብ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በዞኑ የሚገኙ መዋቅሮች የእራሳቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን የገለፁት የሸካ ማህበረሰብ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ስራአስኪያጅ ተወካይና የማስታወቂያ ባለሙያ አቶ ደስታ ዳርቶ ቀጣይ ተቋሙ የእራሱን የገቢ ምንጭ በማሳደግ ውጤታማ ስራ መስራት እንዲችል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል ።

የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በበኩላቸው ባለፋት አመታት የሚዲያ ተደራሽነት ችግር ያለበት አካባቢ መሆኑን ገልፀው ሚዲያ የልማት፣የሰላምና የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ይህን በማጠናከር በዞኑ ሚዲያ ተደራሽ እንዲሆን በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በዚህም የሸካ ማህበረሰብ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ከማቋቋም በተጨማሪ የደቡብ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ማሻ ቅርንጫፍ ወደስራ ገብተዉ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የሰላም የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ በዞኑ የተቋቋሙ የሚዲያ አማራጮች በርካታ ለውጥ እያመጡ መሆናቸውና ለዚህ ከባለስልጣኑ ለተደረገው ድጋፍና ክትትል ምስጋና ያቀረቡት አቶ አበበ አሁንም ቀጣይ ክትትልና ድጋፍ እንዲጠናከር ጠይቀዋል ።

በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የፍቃድና ምዝገባ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አይናለም በየነ በበኩላቸው ተቋሙ ፍቃድ ከወሰደበት ጊዜ ጀምሮ በሚሰራቸው ስራዎች ጥሩ ተሞክሮ ያለበት ራዲዮ ጣቢያ መሆኑን ገልፀው ይህን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

የማህበረሰብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንዲፈታ ማድረግ፣እምቅ ሀብት አካባቢ በመሆኑ ይህን ለአለም ለማስተዋወቅ የማህበረሰብ ራዲዮ መስራት እንዳለበት ገልፀው ከማህበረሰብ ለማህበረሰብ የማህበረሰብ የሚል ሶስት አንኳር ነጥቦች ያለው በመሆኑ የማህበረሰብ ድጋፍና ክትትል መጠናከር አለበት ብለዋል ።

በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የማህበረሰብና የሀይማኖት መገናኛ ብዙሃን ክትትል ምክትል ደስክ ሀላፊ አቶ ሁሰን ሻንቆ የደቡብ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ማሻ ቅርንጫፍና የሸካ ማህበረሰብ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አሁንም ይህን አብሮነት በማስቀጠል የመረጃ ተደራሽነትን ማረጋገጥ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ተቋሙ የውስጥ ገቢ ማሳደግ እንዲችል የማህበረሰብ ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ ፣የአገልግሎት አሰጣጥ እርካታ ደረጃ በማሳደግ ውጤታማ ስራ መሰራት እንዳለበት ፣አጀንዳ ቀርፀው የማህበረሰቡን ችግር መቅረፍ ላይ ሚዲያው መስራት እንዳለበትም አቶ ሁሰን ጠቁመዋል ።

በበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት እየሰጡ ለሚገኙ ሰራተኞች አስፈላጊ ጥቅማ ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ መስራት እንደሚገባ የገለፁት አቶ ሁሰን ቀጣይ ባለስልጣኑ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ የበኩሉን እንደሚወጣም ገልፀዋል ።

ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የተገኙት ባለድርሻ አካላት የቦርድ አባላት ፣የጣቢያው ስራአስኪያጅ ፣የሰው ሃይል ቁጥር ምን ያህል የተሟላ መሆኑንና ቋሚ እና ግዜያዊ ሰራተኞች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ፣ለበጎ ፍቃደኞች አስፈላጊ ድጋፍ ማድረግ ያለበትን ደረጃ አረጋግጠው ዞኑ የሚዲያ ጠቀሜታ በመገንዘብ የተደራጀ የስራ ቦታ በማመቻቸቱ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሚዲያው ዘርፍ መንግስት የያዛቸውን የልማት እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ወሳኝ በመሆኑ ከዚህ በፊት የሚዲያ ተደራሽነት ችግር በዞኑ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ የዞኑ መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በሰራው ስራ ውጤታማ ለውጥ እየተመዘገበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል ።

ተቋሙ እያከናወነ ስላለው ተግባር ሀሳብና አስተያየት ከአድማጮች የተቀበሉ ሲሆን አድማጮችም ተቋሙ ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በመግለፅ አሁንም ይህ አይነት ተግባር ተጠናክረው መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።