ማሻ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ደሬቴድ ማሻ ቅርንጫፍ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚደርሱ የእሳት ቃጠሎ መንስኤዎችን በፎረንሲክ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በዚህም ባለፉት 6 ወራት በፎረንሲክ ከተጣሩ 103 የእሳት ቃጠሎ መንስኤዎች ውስጥ አሥሩ ሆን ተብሎ በሰው አማካይነት የተፈጸሙ ናቸው።
ለመሆኑ ሰዎች ለምን የራሳቸውን ወይም የሌላን ሰው ንብረት ሆን ብለው በእሳት እንዲቃጠል ያደርጋሉ?
የፌደራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ከተማ ደባልቄ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ፥ ፌደራል ፖሊስ በኢትዮጵያ የትኛውም አካባቢ የሚደርሱ የእሳት ቃጠሎ መነሻ መንስኤዎችን በፎረንሲክ ምርመራ የመለየት አቅም ገንብቷል።
ለዚህም ዘመኑን የዋጀ ላቦራቶሪ እና በውጪና በሀገር ውስጥ በዘርፉ አስፈላጊውን ሥልጠና የወሰዱ ባለሞያዎች መኖራቸውን አንስተዋል።
ባለሞያዎቹ የቃጠሎ አደጋ በደረሰበት ስፍራ ፈጥነው በመገኘት ማስረጃ እንደሚሰበስቡ ገልጸው ፥ በቀጣይም ማስረጃዎችን በፎረንሲክ ላቦራቶሪ ኬሚካሎችን በመጠቀም ምርመራ ያካሂዳሉ ብለዋል።
ሁሉም ቃጠሎዎች ምክንያት አላቸው የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ፥ ሆን ተብሎ በሰው አማካኝነት የሚፈጸሙ ቃጠሎዎች ግን ልዩ ትኩረት ይሻሉ ነው ያሉት።
ሰዎች ሆን ብለው ንብረት በእሳት እንዲቃጠልና እንዲወድም ለማድረግ ለራሳቸው የሚያስቀምጧቸው የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉም አስረድተዋል።
በግማሽ ዓመቱ ከተለዩና ሆን ተብለው በሰው ከደረሱ 10 የቃጠሎ መንስኤዎች ውስጥ ከኢንሹራንስ አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት ሲባል የተፈጸሙ መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ሰዎች ኢንሹራንስ ለማግኘት ሲሉ ንብረታቸውንም ሆነ ተሽከርካሪያቸውን የተለያየ ምክንያት ፈጥረው በእሳት እንደሚያቃጥሉ ተናግረዋል።
ሆን ተብሎ የእሳት ቃጠሎ የሚደርስበት ሌላኛው ምክንያት ደግሞ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ለመደበቅና ማስረጃ ለማጥፋት በማለም መሆኑን ጠቁመው ÷ ለአብነትም ቤት ውስጥ በሰው ላይ የግድያ ወንጀል ከፈጸሙ በኋላ ቤቱን በማቃጠል ሰዎቹ በእሳት አደጋ ሕይወታቸው እንዳለፈ የማስመሰል ድርጊት መኖሩን ጠቅሰዋል።
ከፍተኛ የሰነድ ማጭበርበር ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ ኦዲት ሊደረግ ሲታሰብ ሒደቱን ለማቋረጥ እሳት ተነሳ ብሎ ሰነዶችን የማቃጠል ተግባር እንዳለም አንስተዋል።
ሰዎች ከግለሰቦች ጋር ባላቸው የግል ጥላቻ እንዲሁም ይዞታቸውን ሰፋ አድርገው ለማጠር ወይም ግንባታ ለማካሄድ ሲሉ ሆን ብለው ቃጠሎ እንደሚያደርሱም አብራርተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ሆን ተብሎ በሰው አማካይኝት በተፈጸሙ የእሳት ቃጠሎዎች መኖሪያ ቤቶችን እና ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ከ359 በላይ ንብረት ላይ ውድመት መድረሱን አመልክተዋል፡፡
አሁን ላይ የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ አቅም በሰው ሃይልም ሆነ የቴክኖሎጂ አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ፥ የየትኛውንም ቃጠሎ መነሻ መንስኤ የመለየት አቅም አለው ብለዋል።
ስለሆነም ዜጎች ድርጊቱ በምርመራ የሚታወቅ መሆኑን በመገንዘብ አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ሆን ብለው ንብረት ላይ የእሳት ቃጠሎ ከማድረስ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
በግማሽ ዓመቱ ሆን ብለው የእሳት ቃጠሎ በማስነሳት ንብረት እንዲወድም ባደረጉ አካላት ላይ ምርመራ በማጣራት የተለያዩ ርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚኙም አረጋግጠዋል፡፡
የፎረንሲክ ምርመራ የፍትሕ ሥርዓቱ ተአማኒ እንዲሆን እና መሰል ድርጊት የፈጸሙ አካላት ተገቢ ፍትሕ እንዲያገኙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የእሳት አደጋ ሲደርስ የተለያዩ ሃሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት አደጋውን ሁከት ለማስነሳት የሚጥሩ ሃይሎችን ለማስቀረት ፎረንሲክ ምርመራ ሚናው ጉልህ እንደሆነም አንስተዋል።
ኤፍ ኤም ሲ
More Stories
ፑቲን በሩሲያ አየር ክልል ውስጥ ስለተከሰከሰው የአዘርባጃን አውሮፕላን ይቅርታ ጠየቁ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ በአዲሱ ሪፎርም ዕሳቤዎችና በአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ለዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች በቦንጋ ከተማ ስልጠና ሰጠ።
ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ለይፋዊ ስራ ጉብኝት ኮንታ ዞን ገቡ