በአሜሪካ አሪዞና ግዛት ስኮትስዴል አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ የሞትሊ ክሩይ ባንድ ሙዚቀኛ ቪንስ ኒል ንብረት የሆነ የግል አውሮፕላን ቆሞ ከነበረ ሌላ የቢዝነስ ጀት ጋር በመጋጨቱ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በሌሎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለፀ።
ሊያርፍ የነበረው ሌርጀት 35 ኤ የተባለ አነስተኛ የግል አውሮፕላን መንገዱን ስቶ ከሌላ ቆሞ ከነበረ ገልፍ ስትሪም 200 ከተባለ የቢዝነስ ጀት ጋር በመጋጨቱ ነው አደጋው የደረሰው፡፡
የስኮትስዴል ከተማ የእሳት አደጋ መከላከያ ቃል አቀባይ ዴቭ ሮሊዮ፤ በአደጋው የ 1 ሰው ህይወት ማለፉን በ4 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ እና ቀላል ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የግል አውሮፕላኗን ሲያበር የነበረው ፓይለት በአደጋው ህይወቱ ማለፉ ነው የተሰማው ፡፡
የአውሮፕላኗ ባለቤት የሆነው ሙዚቀኛው ቪንስ ኒል በአውሮፕላኗ አለመሳፈሩን እና የሙዚቀኛው የፍቅር አጋር የሆነች ሴት በአደጋው ጉዳት እንደደረሰባት ተነግሯል፡፡
የአሜሪካ የፌዴራል አቬሽን አስተዳደር አውሮፕላኑ እንዴት መስመሩን ስቶ ከሌላ አውሮፕላን ጋር እንደተጋጨ እያጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ አደጋው የተከሰተው የአሜሪካ የአየር ደህንነት ከፍተኛ ምርመራ እየተደረገበት ባለበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡
አሜሪካ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በዋሽንግተን ዲሲ፣ በፊላደልፊያ እንዲሁም በአላስካ በደረሱ የአቬሽን አደጋዎች በርካታ ሰዎች ህወታቸውን አጥተዋል፡፡
More Stories
“አስቸኳይ ፓስፖርት እናሰራላችኋለን” በሚል ሰዎችን ሲያጭበረብሩ ነበሩ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ተያዙ
3ኛው የፓርላማ ዜጎች ፎረም እየተካሄደ ነው
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ እንዲጠናከር ጥሪ ቀረበ