February 23, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ትራምፕ ጾታቸውን የሚቀይሩ አትሌቶች በሴቶች ስፖርት እንዳይሳተፉ የሚያግድ ትዕዛዝ ፈረሙ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጾታቸውን የሚቀይሩ (ትራንስጀንደር) አትሌቶች፤ በሴቶች ስፖርት ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚከለክለውን አስፈፃሚ ትዕዛዝ በትናንትናው ዕለት ፈርመዋል።

ትራምፕ ከ2028ቱ የሎስ አንጀለስ ኦሎምፒክ በፊት ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ጾታቸውን በሚቀይሩ አትሌቶች ላይ ያወጣውን ሕግ እንዲቀይር እንደሚገፋፉም አፅንዖት ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ትዕዛዙን በዋሽንግተን ከሚገኘው የኋይት ሐውስ “ኦቫል ኦፊስ” ጽሕፈት ቤታቸው በደርዘን በሚቆጠሩ ሕጻናት እና ሴት አትሌቶች ተከበው የፈረሙ ሲሆን፤ “በዚህ አስፈፃሚ ትዕዛዝ በሴቶች ስፖርት ላይ ያለው ጦርነት አብቅቷል” ብለዋል።

በተጨማሪም የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ማይክ ጆንሰን እና የሪፐብሊካን ኮንግረስ አባል ማርጆሪ ቴይለር ግሪን በስምምነቱ ላይ መገኘታቸውን የኤፍ ፒ ዘገባ አመላክቷል።

ትራምፕ ትዕዛዙን በፊርማቸው ባጸደቁበት ወቅት፤ “የሴት አትሌቶችን ኩሩ ባህል እንጠብቃለን፣ ወንዶች ሴቶቻችንን እና ልጃገረዶችን እንዲደበድቡ፣ እንዲጎዱ እና እንዲያጭበረብሩ አንፈቅድም። ከአሁን ጀምሮ የሴቶች ስፖርት ለሴቶች ብቻ ይሆናል” ሲሉም ተናግረዋል።

አክለውም፤ “ጾታቸውን የቀየሩ አትሌቶች እርስ በራሳቸው ወይም በወንድ ቡድኖች መወዳደር ይችላሉ” ብለዋል።

ትዕዛዙ አሁን በሥራ ላይ ሲውል፤ የመንግሥት ኤጀንሲዎች ጾታቸውን የቀየሩ አትሌቶች በሴቶች ቡድን ውስጥ እንዲወዳደሩ ለሚፈቅዱ ትምህርት ቤቶች የፌደራል የገንዘብ ድጋፍ መከልከልን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች እንደሚወስዱ ፍቃድ የሚሰጥ መሆኑ ተነግሯል።

“ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ፍትሃዊ የአትሌቲክስ እድሎችን የሚከለክሉ፣ ለአደጋ፣ ውርደት እና ዝምታን የሚዳርጉ እና ግላዊነታቸውን የሚነፈጉ ሁሉንም የገንዘብ ድጋፎች ከትምህርታዊ ፕሮግራሞች መሰረዝ የአሜሪካ ፖሊሲ ነው” ሲል አስፈፃሚው ትዕዛዝ ላይ ይገልጻል።

47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ አሸንፈው ቢሮ እንደገቡ 200 አካባቢ ትዕዛዞች ላይ ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውሳኔ ከሚያስተላልፉባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በሀገሪቱ ለወንድ እና ሴት ጽታ ብቻ እውቅና መስጠት መሆኑን ተናግረዋል።

(አሐዱ ሬዲዮ)