February 23, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የመምህራን አቅም ግንባታ ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የትምህርት ቢሮ ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ በተገኘው የበጀት ድጋፍ በተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ፕሮግራም (CPD) ላይ ለባለሙያዎችና ለመምህራን በቦንጋ ከተማ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል ።

በስልጠናው መግቢያ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊና የመ/ራን ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ቡልቻ የስልጠናው ዓላማ በመ/ራን ልማት ላይ የሚታየውን ማነቆዎች በመለየት መ/ራንን በይዘት፣ በስነ ዘዴና በሌሎች የትምህርት ቤቱ ተጓዳኝ ጉዳዮች ላይ በማብቃትና በማበልፀግ የትምህርት ጥራትን ማምጣትና የተማሪ ውጤትን ማሻሻል እንደሆነ ገልጸዋል ።

ለዚሁም መነሻ በ2015 ዓ/ም በተደረገው የመ/ራን ምዘና ላይ ዝቅተኛ ውጤት ከመመዝገቡም በላይ የአቅም ውስንነት፣ ይዘትን የመገንዘብና ይዘቱን ወደ ተማሪዎች ከማስተላለፍ ጉድለት በመታየቱ መምህራን ያሉበት ደረጃወን ተለይቶ በተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና አቅምን መገንባት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ነው ያሉት አቶ ማርቆስ።

በመሆኑም የመምህራን ሙያ ማሻሻያ ጉዳይ የሚያቋርጥ ሂደት ሳይሆን በተከታታይ በስራ ላይ ስልጠና በመስጠት የመምህራንን አቅም ማጎልበቻ በመሆኑ

አቅዶ በመስራት በተከታታይ ስራ ላይ ስልጠና በመስጠት ወደ ሁሉም ት/ቤቶች ወርዶ ተግባራዊ መደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል ።

የትምህርት ጉዳይ የትውልድ ግንባታና ለሀገር ግንባታ መሠረት በመሆኑ የመምህራንን አቅም በማጎልበት የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ሆነ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ በመሆኑ ሰልጣኞች በትኩረት በመከታተል በማነቆዎች ላይ በመወያየት ለለወጥ እንዲተጉ አሳስበዋል ።

በስልጠናው ላይ በተከታታይ የትምህርት ማሻሻያ ፕሮግራም ውጤት ያስመዘገቡ ትምህርት ቤቶች ተሞክሮ ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ሲሆን በመቀጠልም በቦንጋ መምህራን ኮለጅ በቀጣይ መምህራን አቅም መገንቢያ ላይ ስልጠና እንደሚሰጥ የወጣው መርሃ ግብር ያስረዳል።

በስልጠናው ላይ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ፣ ከዞኖች የመጡ የመ/ራን ልማት ዘርፍ አስተባባሪዎች፣ ር/መ/ራን፣ ሱፐርቪዥን ባለሙያዎች፣ መምህራንና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።