February 1, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የአገው ፈረሰኞች በዓል ለፌስቲቫል ቱሪዝም ገቢ

የአገው ፈረሰኞች በዓል ለፌስቲቫል ቱሪዝም ገቢ ተቋዳሽ ለመሆን ያመቻቻል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ይገልጻሉ።

ኃላፊዋ 85ኛው የአገው ፈረሰኞች ማህበር ምስረታ በዓልን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዛሬ አራት ዓመት 81ኛውን የአገው ፈረሰኞች በዓል ለማክበር ዕድሉን አግኝቼ ፣ ተደምሜም ነበር ብለዋል።

በዓሉ ላይ የተዘጋጁ የተለያዩ እና ያልተለመዱ ምግቦች፣ ሙዚቃ፣ አልባሳት፣ ከፈረስ ትርዒቱ ጋር ተደምሮ ድንቅ ድባቡ እንዳለው አስታውሰዋል።

ሴት ፈረሰኞችም የዚህ አካል ሆነው ሳይ ከፍተኛ አድናቆት ተሰምቶኝ ነበር ያሉት ኃላፊዋ፤ እንደ ሀገር ያሉት ኹነቶች ሲመነዘሩ ብዙ ዕድሎችን እንደሚያመቻቹ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ያሉንን ዕሴቶች እያዳበርን ማሳደግ የምንችልበትን ዐቅም ይፈጥራሉ ብዬ አምናለሁ ሲሉ አመልክተዋል።

ዛሬም 85ኛው የአገው ፈረሰኞች ማህበር ምስረታ በዓል ሲከበር ብዙ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች እንደሚታደሙ እምነታቸውን ገልጸው፤ አካባቢውም ነቅቶ ሰላሙን በመጠበቅ በዓሉን ከዓመት ዓመት ማከናወን መቻሉ የወደፊት ዕድሉን እያጠናከረ ነው ብለዋል።

የአገው ፈረሰኞች ማህበር ምስረታ በዓልን ለፌስቲቫል ቱሪዝም ገቢ ተቋዳሽ ለመሆንም ያመቻቻል ሲሉ አስገንዝበዋል።