ማሻ፣ ጥር 6፣ 2017 (ደሬቴድ ማሻ ቅርንጫፍ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 41ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ውሳኔዎቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማህበር ጋር ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግስት አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የ53,300,000.00 ኤስ.ዲ.አር እና ለፋይናንስ ዘርፍ ማጠንከሪያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የ525,700,000 ኤስ.ዲ.አር የፋይናንስ ድጋፍ እና ብድር ስምምነቶችን ለማጽደቅ በቀረቡ 2 ረቂቅ አዋጆች ላይ ነው፡፡
ሁለቱም ብድሮች ከወለድ ነጻ፣ 0.75% የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልባቸው ሆኖ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ውስጥ ተከፍለው የሚጠናቀቁ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ ብድሮቹ ከሀገራችን የብድር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆኑን በማረጋገጥ ረቂቅ አዋጆቹ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2. ቀጥሎም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብን ለማሻሻል በወጣ ደንብ ላይ ነው፡፡
የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብ ቁጥር 517/2014 ተግባራዊ እየተደረገ ቢሆንም ደንቡ ከመውጣቱ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ በተለያዬ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች የአፈጻጸም ችግር እያጋጠማቸው በመሆኑ የደንቡ ድንጋጌዎች ግልጽ እንዲሆኑ ለማድረግ የቀረበው ማሻሻያ ደንብ ላይ ውይይት ከተደረገ ቦኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
3. የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደርን ለማፍረስ የቀረበ ረቂቅ ደንብ ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ ነው፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የፕራይቬታይዜሽን ስራዎች ወደ ዕዳ እና የሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ተላልፈው እንዲከናወኑ ለማስቻል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደርን በሕግ አፍርሶ መብቶቹንና ግዴታዎቹን ለኮርፖሬሽኑ ማስተላለፍ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ደንቡ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በስፋት ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
(ኤፍ ኤም ሲ)
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።