ማሻ፣ ጥር 6፣ 2017 (ደሬቴድ ማሻ ቅርንጫፍ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ጉባዔ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ተፈጻሚነት የሚኖረው የንብረት ታክስ አዋጅን በአራት ተቃውሞ በአስር ድምጸ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
የንብረት ታክስ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለማስፈን፣ አገልግሎትን በተሻለ ጥራት ለማቅረብና የመሰረተ ልማት ማሻሻያዎችን በቀጣይነት ለመተግበር የሚወጣውን የኢንቨስትመንት ወጪ በንብረት ዋጋ ማደግ ምክንያት በሚጣል ታክስ አማካኝነት ለመሰብሰብ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡
የፀደቀው አዋጅ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች ተፈጻሚነት የሚኖረው ሲሆን÷ ክልሎች አዋጁን መሰረት በማድረግ ከተጨባጭ ሁኔታቸው ጋር በተጣጣመ አኳኋን የየራሳቸውን የንብረት ታክስ ህግ እንዲያወጡ ያስችላልም ተብሏል።
የምክር ቤት አባላት አዋጁ ላይ የፌደራልና የክልል መንግስት ተቋማት እንዲሁም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከንብረት ታክስ ነጻ የተደረጉ ተቋማት መሆናቸውን በማንሳት የሐይማኖት ተቋማት ለምን አልተካተቱበት ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
እንዲሁም ከንብረት ታክስ የሚገኘው ገቢ ለምን አይነት መሰረተ ልማቶች እንደሚውል በግልጽ አዋጁ ላይ እንዳልተቀመጠ ጠቅሰው÷ መብራት፣ ውሃና ሌሎችም የአስተዳደር አገልግሎቶች ላይ የሚስተዋለው ችግርም እንዲስተካከል ጠቁመዋል፡፡
የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ÷ በከተሞች በንብረት ታክስ ተብሎ ባይከፈልም ለመሰረተ ልማቶች ህብረተሰቡ እየተመካከረ የሚያዋጣው ገንዘብ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
(ኤፍ ኤም ሲ)
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።