የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ውጤታማነት የበለጠ ለማሳደግ የፋይናንስ ዘርፉ ቅንጅታዊ አሰራር ይጠናከራል ሲሉ የገንዝብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ አስታወቁ።
የፌዴራልና የክልሎች የፋይናንስ፣ የገቢዎችና የፕላን ምክክር መድረክ በጅማ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን በምክክሩ ላይ የዘርፉ ከፍተኛ አመራር አባላት እየተሳተፉ ነው።
በዚሁ ወቅት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፥ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተቀናጀ መልኩ እየተተገበረ ውጤታማ ሆኖ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የምክክሩ ዋና ዓላማም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሚጠይቀው መልኩ የዘመነ የፋይናንስ ስርዓትን ለመገንባት ብሎም የወደፊት የስራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ውጤታማነት የበለጠ ለማሳደግ የፌዴራልና የክልሎች የፋይናንስ ዘርፍ ተቋማት ቅንጅት የበለጠ እንደሚጠናከር አመልክተዋል።
”ህዝቡንና ባለሀብቱን በማስተባበር ገቢያችንን ማሳደግ አለብን” ያሉት ሚኒስትሩ ይህንንም የፌዴራልና የክልሎች የዘርፍ ተቋማት ተናበው ሊሰሩት ይገባል” ብለዋል።
በተለይም ገቢን በአግባቡ መሰብሰብና ለታለመለት የልማት ግብ በማዋል ረገድ በርካታ የቅንጅት ስራዎች ይጠበቃሉ ሲሉም ገልጸዋል።
ባለፋት ስድስት ዓመታት የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን አውስተው፥ የሚሰበሰበው ገቢ በኢኮኖሚው እድገት ልክ አለመሆኑን አስረድተዋል።
በአጠቃላይ የገቢ አሰባሰብና የፋይናንስ ስርዓቱን በማሻሻል እና በማዘመን የአገርን ኢኮኖሚ ማሳደግ የሁሉንም ትብብር የሚፈልግ ስራ ነው ብለዋል።
በምክክር መድረኩ ላይም የኢኮኖሚ ማሻሻያውን አተገባበርና የፋይናንስ ስርዓቱን ከማዘመን አኳያ ውይይት ተደርጎ የስራ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም አመላክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።