January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት እና ነባሮቹን ዓለም አቀፍ ደረጃ በማሳደግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።

የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የፌደራልና የክልል የዞን አመራር አባላት በተገኙበት በታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ተከብሯል።

ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ በዚሁ ወቅት፥ ኢትዮጵያ ላሊበላን መሰል ዓለምን ያስደመሙ የተፈጥሮና ታሪካዊ መስህቦች ባለቤት ናት ብለዋል።

በርካታ የቱሪስት መስህቦቿ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት የቱሪስት መስህቦችን የማልማትና አዳዲሶችን የመገንባት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እያከናወነ ነው ብለዋል።

የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን ማብዛት፣ የቱሪዝም ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትና የውጪ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በዓላትና ባህላዊ ክዋኔዎች እሴታቸው ተጠብቆ እንዲከበሩና በስፋት እንዲተዋወቁ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑም አክለዋል።

አማራ ክልል የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን፣ የጎንደር አብያተ መንግሥት፣ የሰሜን ተራሮች፣ ጎርጎራ፣ የጣና ሃይቅ ደሴቶችና ገዳማት፣ ጢስ አባይ ፏፏቴና መሰል ድንቅ መዳረሻዎች ባለቤት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የቱሪስት መዳረሻዎቹ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳቸው የላቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የላሊበላ ኪነ ሕንፃዎች ያኔ ቀርቶ በዚህ ዘመን ለመገንባት የሚከብዱ እንደሆኑ ነው ያነሱት።

የላሊበላ መካነ ቅርስ መዳረሻን ለማልማትና ከነሙሉ ውበቱ ለቀጣይ ትውልድ ለማሻገር መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

እስካሁንም በመካነ ቅርሱ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና ድልድዮች እና የመታጠቢያ ቤት ግንባታዎች እንዲሁም አስጎብኚ ማህበራትን የሚደግፉ ስራዎች ተከናውነዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።