January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኮሪደር ልማቱ የከተሞችን ዕድገት ከግምት ያስገባ ነው – አቶ ሙስጠፌ መሀመድ

ማሻ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ደሬቴድ ማሻ ቅርንጫፍ) መንግሥት እየተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ዕድገት ከግምት ያስገባ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ላለፉት ሁለት ቀናት ባካሄደው ስብሰባ በተለያዩ ሀገራዊና የፓርቲው አጀንዳዎች ላይ ተወያይቷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ፓርቲው በውይይቱ የከተሞች የኮሪደር ልማት በተያዘለት እቅድ መሰረት በውጤታማነት እየተተገበረ መሆኑን ተመልክቷል ብለዋል።

መንግሥት እየተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ዕድገት ከግምት ማስገባቱን ገልጸው፤ ንቅናቄው በሚቀጥሉት 30 ዓመታት እስከ 70 በመቶ የዓለም ህዝብ ከተሜ ይሆናል የሚለውን ታሳቢ ያደረገና ዘመናዊ የክትመት ስርዓትን የመገንባት ግብ ያስቀመጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት አድማሱን በክልል ከተሞች ያሰፋው የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ኤሌክትሪክ፣ ድልድይ፣ የአስፋልት መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን መገንባት መሆኑን ገልጸው፥ ይህም የእሳቤውን ስትራቴጂካዊነት በግልፅ የሚያመላክት መሆኑን አንስተዋል።

የኮሪደር ልማት በአዲስ አበባ በመጀመሪያው ምዕራፍ የተሟላ መሰረተ ልማት፣ ምቹ የመኖሪያና መዝናኛ ሥፍራዎችን በመገንባት በመዲናዋ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎም በክልል ከተሞች ገቢራዊ መደረጉ የኢትዮጵያን የክትመት እንቅስቃሴ እያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አዳዲስ እሳቤዎችና ፈጠራዎች መልካም ነገር ይዘው ሲመጡ ውጤታቸው በረዥም ጊዜ ሊታይ የሚችል ቢሆንም የኮሪደር ልማት ስኬቶቻችን ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የመፈጸም አቅማችንን ያሳዩ ናቸውም ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ በምሥራቅ አፍሪካ ፈጣን እድገት ካስመዘገቡ ከተሞች መካከል ጅግጅጋ ቀዳሚዋ መሆኗን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ ህብረተሰቡ የኮሪደር ልማቱን ጥቅም በውል ተገንዝቦ በባለቤትነት እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተሰሩ ፕሮጀክቶች ውብ እና ጎብኚዎችን የሚስቡ በመሆናቸው የቱሪዝም እንቅስቃሴውን እያሳደገው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ከተሞችን ዘመናዊ ለሰው ልጅ ምቹና ተስማሚ በማድረግ ጎብኚዎችን ለመሳብ ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡