January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በሥራ ዕድል ፈጠራ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ለዘርፉ በቴክኖሎጂ ታግዞ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮዽያ ህዝቦች ክልል መንግስት ሥራና ክህሎት ቢሮ ለሸካ ዞን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በአዲሱ ሪፎርም ዕሳቤዎችና የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ለዘርፉ አመራርና ማኔጅንት አባላት ጋር በቴፒ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ በሪፎርሙ ዙሪያ ሰነድ ያቀረቡት የቢሮዉ ምክትል ኃላፊና የስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አየለ በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ተገቢዉን የገበያ ትስስር ለሁሉም መፍጠር እንዲቻል ስራዉ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ለዜጎች ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥተዉ መስራት እንደሚገባቸዉ ተናግረዋል።

በተዋረድ የአመራሩ ድጋፍና ክትትል ለእንተርፕራይዞች አናሳ መሆኑን ገልጸዉ ፣ በተለይ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሰዉ ኃይልና በቁሳቁስ በተገቢዉ ያለመደራጀቱ፣ በስራ ላይ ያለዉም የሰዉ ኃይል በተገቢዉ አገልግሎት ያለመስጠቱና የመረጃ አያያዝ ስርዓቱ ደካማ መሆኑ ማነቆ እየፈጠረ እንዳለም አንስተዉ ይህንንም ለማረም ሁሉም ተቀናጅቶ በትኩረት ልሰራ እንደሚገባም አንስተዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ለሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባር ስኬት የሰዉ ኃይልና ቁሳቁስ እንድሟላ ጠይቀዉ የሚጠበቅባቸዉን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸዉን ጠቁመዋል።

በማጠቃለያዉ ለስራ ዕድል ፈጠራ ሁሉም የሚመለከታቸዉ አካላት በቁርጠኝነት ልሰሩ እንደሚገባቸዉ ከመድረኩ የተገለጸ ሲሆን በአካባቢዉ ያለዉን ጸጋ ታሳቢ ያደረገ የፈጠራ ስራን ልጎለብት እንደሚገባና ለዚህም በተለይ ስራ ፈላጊዎችን ለይቶ በማደራጀት ረገድ በትኩረት በመስራት ለዉጥ ማምጣት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአንድ ማዕከልን የመደገፍ ስራ ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራም ተገልጿል።