62 መንገደኞችን እና አምስት የበረራ ሰራተኞችን ኣሳፍሮ ከአዘርባጃን ወደ ሩሲያ ሲበር የነበረው ኢምብራኤር አውሮፕላን ካዛኪስታን ውስጥ አክታው ከተማ አቅራቢያ መከስከሱን ሮይተርስ የካዛኪስታን ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።
ባለስልጣናቱ እንደገለጹት 12 ሰዎች ከአደጋው በህይወት ተርፈዋል። አብዛኞቹ መንገደኞች ሳይሞቱ እንደማይቀር ተሰግቷል።
በአዘርባጃን ኤየርላየንስ የሚተዳደረው አውሮፕላን በእሳት ተያይዞ ከመሬት ጋር ሲጋጭ እና ወፍራም ጥቁር ጭስ ሲጨስ ያልተረጋገጡ ቪዲዮዎች አሳይተዋል።
የማዕከላዊ እስያዊቷ ሀገር የአደጋ ጊዜ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የእሳት አደጋ አገልግሎት እሳቱን ማጥፋቱን እና በህይወት የተረፉት በቅርብ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጿል።
የአዘርባጃን ኤየርላየንስ የበረራ ቁጥሩ ጄ2-8243 የሆነው ኢምብራኤር 190 አውሮፕላን ከባኩ ወደ ሩሲያዋ ቺቺኒያ ግዛት ዋና ከተማ ግሮንዜ እየበረረ ነበር። ነገርግን ከካዛኳ አክታው ከተማ ለመድረስ ሶስት ኪሎሜትር ሲቀረው በድንገት ለማረፍ ተገዷል።
የሩሲያ መገናኛ ብዙኻን አውሮፕላኑ አቅጣጫውን የቀየረውን በግሮንዜ በነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ምክንያት ነው ብለዋል።
የአዘርባጃን ባለስጣናት የቴክኒክ ችግርን ጨምሮ የአደጋው መንስኤ ምክንያቶችን ለማወቅ ምርመራ ጀምረዋል።
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።