December 18, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ የሚፈቅድ አዋጅ ጸደቀ

ማሻ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ደሬቴድ ማሻ ቅርንጫፍ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባው የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ የሚፈቅድ የባንክ ሥራ አዋጅን እና የብሔራዊ ባንክ አዋጅን መርምሮ አፅድቋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምቤት በዛሬው እለት ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ነው የብሔራዊ ባንክ አዋጅንና የባንክ ሥራ አዋጅን ያፀደቀው፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ የምክር ቤት አባላት ላነሱት ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ÷ የብሔራዊ ባንክ አዋጅ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተረጋጋ ሆኖና ጥራቱን ጠብቆ እንዲሄድ ያስችላል ብለዋል፡፡

አዋጁ የባንኩን ዓላማ በግልጽ እንዳስቀመጠ ገልጸው÷ የባንኩ ዋና ሥራ በኢትዮጵያ የዋጋ መረጋጋት እንዲኖር ማስቻልና የፋይናንስ ሥርዓቱ ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም በኢትዮጵያ ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽዖ ማድረግ የባንኩ ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አዋጁ ባንኩ እንዲዘምንና በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ከሚኖሩ ለውጦች ጋር እንዲጣጣም እንዲሁም የቁጥጥር አቅሙን እንዲያጎለብት ያስችለዋል ነው ያሉት፡፡

የባንኩን አደረጃጀት፣ ዓላማና ተግባር፣ ስለ ብሔራዊ ባንክ አሥተዳደር፣ ባንኩ ከመንግሥትና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ስለሚኖረው ግንኙነትና ሌሎችንም ድንጋጌዎች አዋጁ ማካተቱን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የውጭ ሀገር ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ የሚያስችል የባንክ ስራ አዋጅን መርምሮ በሶስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡

አዋጁ የባንክ ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት እንዲደረግ፣ ከዚህ በፊት በመንግስት የተወሰነውን የፖሊሲ ውሳኔ ወደ ተግባር ለማሸጋገር፣ የውጭ ባንኮችና ኢንቨስተሮች በዘርፉ ተሰማርተው ለኢኮኖሚው እድገት ቀጣይነት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ያስችላልም ተብሏል፡፡