December 18, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር መሆኑ ተገለጸ

ማሻ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ደሬቴድ ማሻ ቅርንጫፍ) የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ ቁልፍ የሰላምና የልማት አጋር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

በሚኒስትሩ የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑክን ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት አምባሳደሮችና ተወካዮች እየተሳተፉ የሚገኙበት የኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት የስትራቴጂክ አጋርነት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷ የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ ቁልፍ የሰላምና የልማት አጋር መሆኑን ገልጸው ውይይቱ በሰላምና ጸጥታ፣ በኢኮኖሚ ልማትና በባለብዙ ወገን ትብብር ላይ የሚያተኩር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሕብረቱ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግም እና ትብብሯን ለማጠናከር ዘርፈ-ብዙ ጥረቶች ማድረጓንም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ ማሳደግ ብሎም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊስ ማሻሻያ ገቢራዊ ማድረጓንም ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገር በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ሚና እንዳላት የገለፁ ሲሆን÷ ሕብረቱ በቀጣናው ሰላምና ደኅንነት እንዲሰፍን ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው÷ ኢትጵያና የአውሮፓ ሕብረት ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደ በፈረንጆቹ 2016 የስትራቴጂክ አጋርነት ትብብር መፈራረማቸውን አስታውሰዋል፡፡