በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የይዞታ ማስተካከል ቡድን መሪ የሆነ አሸብር አበባው ታደሰ የተባለ ግለሰብ መረጃ በማጉደል፣ በሥልጣን ያለአግባብ በመገልገል እና ጉቦ በመቀበል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገልጿል።
የወ/ሮ ሙሉ ካህሺን ሕጋዊ ወኪል የሆኑት አቶ ደራራ ዲንሳ ኢረና በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 የሚገኝ የቦታ ይዞታቸው በመሬት ይዞታ ምዝገባ ኤጀንሲ እንዲረጋገጥላቸው ለአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ያመለክታሉ።
ይህን ተከትሎም ተጠርጣሪው የማይገባ ጥቅም በመፈለግ ከአመልካች ማኅደር ላይ መረጃ በማጉደል እና ጉዳያቸውን በማጓተት ሲያጉላላቸው ከቆየ በኋላ መረጃውን አሟልቶ ወደሚመለከተው አካል ለመላክ 1 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ጉቦ መጠየቁን የምርመራ ቡድን ደርሶበታል።
ባለጉዳዩ አቶ ደራራ ዲንሳ የተጠየቁትን ገንዘብ በአዋሽ ባንክ ሂሳብ ቁጥር 01320082310801 ወደ ተጠርጣሪው የንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር 1000218526121 ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ያስገቡ መሆናቸውን ሕዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም ለምርመራ ቡድኑ ጥቆማ አቅርበው ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ሊውል መቻሉን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።
የምርመራ ቡድኑ የተጠርጣሪውን የእምነት ክህደት ቃል በመቀበል፣ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ እስከ ሕዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የ10 ቀን የምርመራ ማጣሪያ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት መፍቀዱ ተገልጿል።
EBC
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።