November 24, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ግብጽ ሁለተኛ ዙር ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳርያ ለሶማሊያ ድጋፍ ማድረጓ ተነገረ

በሶማሊላንድ እና በአዲስ አባባ መካከል የተፈረመውን የወደብ ስምምነት ተከትሎ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በኩል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት እየተባባሰ ይገኛልከፍተኛ መጠን ያለው ከባባድ የጦር መሳሪያዎች የጫነ የግብጽ ግዙፍ ወታደራዊ የጭነት መርከብ ሞቃዲሾ ወደብ መድረሱ ተሰምቷል፡፡ነሀሴ ወር ላይ ካይሮ በሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖች ካደረገችው የጦር መሳርያ ድጋፍ ቀጥሎ ሁለተኛ በሆነው ድጋፍ የአየር እና የታንክ መቃወሚያዎችን ጨምሮ ሌሎች ከባድ የጦር መሳርያዎች የተካተቱበት መሆኑን ሮይተርስ አስነብቧል፡፡ ከግብጽ የተላኩትን የጦር መሳርያዎች ከትላንትናው እለት ጀምሮ ከሞቃዲሾ ወደብ የማራገፍ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ሲነገር፤ ወደ ሀገሪቱ መከላከያ ሚንስትር መስርያ ቤት እና በአካባቢው ወደሚገኙ የጦር ካምፖች ጦር መሳርያዎቹን እየተጓጓዙ ነው ተብሏል፡፡ ይህን ተከትሎም ወደቡ እና ዋና ዋና መንገዶች ለንግድ እና ለሲቪሊያን እንቅስቃሴዎች ዝግ መደረጋቸውን ዘገባው ጨምሮ አስነብቧል፡፡ በሶማሊላንድ እና በኢትዮጵያ መካከል የወደብ የመግባብያ ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ የአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ ግንኙነት መሻከሩ ይታወሳል፡፡ በዚህም የአባይ ውሀን ከመቆጣጠር ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ጋር ቆየት ያለ ባላንጣነት ያላት ካይሮ ወደ አፍሪካ ቀንድ እየቀረበች እንደምትገኝ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በቀጣይ የሚኖረው አዲስ የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር ላይ የኢትዮጵያን ወታደሮች መካተት አልቀበልም ያለችው ሶማሊያ ግብጽ በሰላም አስከባሪ ሀይሉ ውስጥ እንድትሳተፍ ፍላጎቷ መሆኑን ተናግራለች፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘም በተለያዩ ዙሮች የሚሰማሩ እስከ 10 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮቿን በአትሚስ የሰላም አስከባሪ ውስጥ የማሳተፍ ፍላጎት እንዳላት ካይሮ ይፋ አድርጋለች፡፡ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ትብብር የፈጸመችው ግብጽ በአካባቢው ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እና ውክልና እንዲኖራት በሰፊው በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኝ ዘገባው አካቷል፡፡ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት እየተባባሰ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ግብጽ በቀጠናው እደረገችው ያለው ወታደራዊ እንቅስቀሴ በአካባቢው ተጨማሪ አለመራጋጋትን ሊያስከትል እንደሚችል ተንታኞች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ ነሃሴ 2016 ዓ.ም c-130 የተባሉ ሁለት የግብፅ ወታደራዊ አውሮፕላኖች በአደን አዴ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሳቸው በተነገረበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ተቃውሞውን አሰምቶ ነበር፡፡አዲስ አበባ በውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ “የሶማሊያ መንግስት ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ከማጠናከር ይልቅ ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ሲል መውቀሱ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ መሰል እንቅስቃሴዎችን እጇን አጣጥፋ በዝምታ አትመለከትም ሲል አቋሙን አንጻባርቋል፡፡ሮይተረስ በአዲሱ የጦር መሳርያ ድጋፍ ዙርያ ከግብጽ እና ኢትዮጵያ መንግስታት ተጨማሪ መረጃ ለማግኝት ያደረኩት ጥረት አልተሳካም ብሏል፡፡

AL AIN

You may have missed