October 4, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ለናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ሙሉ ትግበራ በጋራ ለመንቀሳቀስ ተስማሙ

በኒውዮርክ እየተካሄደ ካለው የ.ተ.መ.ድ. 79ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን፥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ራምዳን ሞሀመድ አብዱላህ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል። ሚኒስትሮቹ ሁለቱ አገራት በናይል ተፋሰስ ፍትሃዊ እና እኩል ተጠቃሚነት ላይ ባላቸው ወጥ አቋም ዙሪያ ሀሳብ ተለዋውጠዋል። አምባሳደር ታዬ፥ ደቡብ ሱዳን የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በፓርላማ ማፅደቋን በማውሳት ራምዳን ሞሀመድ አብዱላህን እንኳን ደስ ያለዎት ብለዋቸዋል። የደቡብ ሱዳን ፓርላማ ስምምነቱን በማጽደቁ የአገሪቱ ሕዝብ በናይል ተፋሰስ በፍትሀዊነት እና እኩል ተጠቃሚነት ላይ ያለውን መብት ያስከበረ መሆኑን አምባሳደር ታዬ ገልጸዋል። በውይይቱ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ሙሉ ትግበራ በጋራ ለመንቀሳቀስ መስማማታቸውን የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል። ደቡብ ሱዳን የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍን በፓርላማ አጽድቃ ለአፍሪካ ኀብረት ማቅረቧን ተከትሎ፤ ኡጋንዳ እ.ኤ.አ. በጥቅምት አጋማሽ የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽንን መመሥረት የሚያስችለውን ሁለተኛውን የናይል ጉባዔ ለማዘጋጀት ያሳየችውን ቁርጠኝነት መደገፏ ይታወሳል።

EBC