November 22, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በኢትዮጵያ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዘ ሰው የለም – ጤና ሚኒስቴር

በኢትዮጵያ እስከ አሁን ድረስ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዘ ሰው አለመኖሩን ጤና ሚኒስቴር አረጋገጠ፡፡ዛሬ የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ተቋም (አፍሪካ ሲ ዲ ሲ) ባወጣው መግለጫ÷ በ13 የአፍሪካ ሀገራት 2 ሺህ 863 ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ መያዛቸውን እና 517 ያህሉ ሕይወታቸው ማለፉን አሳውቋል፡፡ይህን ተከትሎም በሽታው የሕብረተሰብ ጤና አኅጉራዊ ደኅንነት ስጋት ነው ማለቱን የጤና ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት የጋራ ርምጃ የሚጠይቅ መሆኑም ተጠቁሟል።በኢትዮጵያም ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በሞያሌ እና ሌሎች የመግቢያ ቦታዎች የቁጥጥርና ማጣራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ነው ጤና ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡ሚኒስቴሩና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቅርበት ክትትል እያደረጉ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷ እስከ አሁንም በኢትዮጵያ በበሽታው የተያዘ ሰው አለመኖሩ ተረጋግጧል፡፡በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች ከሚያሳዩአቸው ዋና ዋና ምልክቶች መካከል÷ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የዕጢ እብጠት፣ የጡንቻ እና የጀርባ ህመም፣ ሽፍታ፣ የቆዳ ቁስለት እንዲሁም የአቅም ማጣት ይጠቀሳሉ፡፡ምልክቶች መከሰታቸው የተረጋገጠ እና በቅርቡ በሽታው ወደ ተከሰተባቸው ሀገሮች የጉዞ ታሪክ ያለው ሰው በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራና እንክብካቤ ማግኘት እንዳለበት ሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡በሽታው በቀጥታ ከሰው ወደ ሰው በንክኪ የሚተላለፍ እንደመሆኑ መጠን በመግቢያና መውጫ ኬላዎች አካባቢ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ የተጠናከረ የቁጥጥርና መከላከል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያስታወቀው፡፡ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች የሚያሳይ ማንኛውም ሰው በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም ሪፖርት ማድረግ ወይም በ952 እና 8335 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ ማድረግ የሚቻል መሆኑም ተመላክቷል፡፡

FBC

You may have missed