October 4, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ለሀገርና ለትውልድ የሚተርፉ ባህላዊ ስርዓቶችንና ወጎችን ማስቀጠል ሚናው የጎላ መሆኑ ተጠቆመ

የሸካቾ ባህላዊ አስተዳደር ስርዓት ከ140 ዓመታት በኃላ የካቲት 25/2016 ዓ/ም ከተካሄደው ሹመት ወዲህ የተከወኑትን ተግባራት ሪፖርትና ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች ዙሪያ በአንድራቻ ወረዳ በጌጫ ከተማ ውይይት ተካሂዷል ።የንጉሥ ተቺ ቀጆቺ 17ኛው የሸካቾ ብሄረሰብ የንግስና በዓለ ስመትን ተከትሎ በንጉሡ ባለፉት አራት ወራት የተከወኑ ተግባራት ሪፖርት በአቶ ኪዳነ አገሎ በወረዳው ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ጽ/ቤት ባለሙያ ሰነድ ቀርቧል። ።በንጉሡ የተዘጋጀው ሪፖርት እንደሚያስረዳው የካቲት 27/2016 ዓ/ም ከበዓለ ስመት ማግስት ጀምሮ በርካታ አቤቱታዎች መፍታት መቻላቸው በዝርዝር ቀርቧል።1,022 ቅሬታዎች እስካሁን የቀረቡ ስሆን 791 ምላሽ ስያገኙ 231 ቅሬታዎች ደግሞ በሂደት ላይ እንደሚገኙ በሰነዱ ተብራርቷል ።ከቀረቡት አቤቱታዎች ክህደት የተፈጸመባቸው ፣በብድር የዘገዩና በህግ አግባብ ካልተመለሱ ገንዘብ 14,651,390 (አስራ አራት ሚሊዮን ስድስት መቶ አምሳ አንድ ሺ ሶስት መቶ ዘጠና ብር) ለባለቤቶቹ ማስመለስ መቻሉም ተጠቁሟል ።ከዚህም ባሻገር አወዛጋቢ የፍርድ ቤት ክርክሮች፣መሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች፣በፍ/ቤት በወንጀል ተከሰው የተሰወሩትን እጅ እንዲሰጡ ከማድረግ ጀምሮ በርካታ አቤቱታዎችን እስካሁን መፍታት መቻሉ ተገልጿል ።የሚቀርቡት አቤቱታዎች ከወረዳው ፣ከዞኑና ከክልሉ አልፎ ከአዲስ አበባና ከሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች ቀርበው ምላሽ ማግኘታቸውም ተብራርቷል ።በቀን በአማካይ 9 አቤቱታዎች እስካሁን የሚቀርቡ ስሆን ከ1973 ዓ/ም እስከ 2016 ዓ/ም ያሉ አቤቱታዎች ባለፉት አራት ወራት ውስጥ መመዝገቡም በሰነዱ ተካቷል ።በቀጣይ ከሸካቾ ባህልና ወግ ያፈነገጡ ልማዳዊ ድርግቶች የሚወገዙበት ስርዓት #ሼሮ(ትሞ)ና በ2017 ዓ/ም የሚከበር የሸካቾ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል #ማሽቃረ ባሮ#አከባበር ዙሪያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ።ንጉሥ ተቺ ቀጆቺ በበኩላቸው ከዕለቱ ጀምሮ በዝርዝር የቀረቡት አዳዲስ ባህላዊ ህጎች እምነትንና ህገመንግስታዊ ስርዓትን የማይቃረኑ መሆን እንዳለባቸው አብራርተዋል ።በብሄረሰቡ ዘንድ የሚተገበሩ አዳዲስ ህጎች ለመንግስት ፣ለሀገርና ለትውልድ የሚተርፉ በመሆናቸው ስርዓቶችንና ወጎችን ለማስቀጠል እስከታችኞቹ መዋቅር ድረስ በሰፊው ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግም ጠይቀዋል።በቀጣይ በ2017 ዓ/ም የሚከበረውን የሸካቾ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል ለማክበር ሁሉም ከወዲሁ እንዲረባረብም ጠይቀዋል።ተሳታፊዎች በበኩላቸው እየተከወኑ ያሉትን ተግባራት አድንቀው መጨመር አሉባቸው ያሉትንም ጉዳዮች አንስተው ውይይት ተካሂዷል ።ክቡር ንጉሥ ተቺ ቀጆቺ፣የምክሬቾ አባላት፣ጎሳ መሪዎች ፣የሀገር ሽማግሌዎች ፣የሀይማኖት መሪዎች፣የወጣቶችና የሴቶች ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት በመድረኩ ተሳትፈዋል ።በቀጣይ በዞኑ በሚገኙት መዋቅሮች በዕለቱ ጉዳዮች ዙሪያ መድረክ ተፈጥሮ ውይይት እንደሚደረግባቸውም ተጠቁሟል።

የዘገበው የአንድራቻ ወረዳ መ/ኮ/ጉ/ጽ/ቤት ነው ።