January 23, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኢትዮጵያ ቆይታችን አስደሳች እና ሀገሪቱም በፈጣን ለውጥ ላይ መሆኗን የተገነዘብንበት ነው – የናይጀሪያ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋቾች

የኢትዮጵያ ቆይታችን አስደሳች እና ሀገሪቱም በፈጣን ለውጥ ላይ መሆኗን የተገነዘብንበት ነው ሲሉ የናይጀሪያ የቀድሞ ታላላቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ተናገሩ፡፡የቀድሞው የናይጀሪያ የእግር ኳስ ኮከብ ንዋንኩ ካኑን ጨምሮ የቀድሞ የአህጉሪቱ ታላላቅ ተጫዋቾች በአዲስ አበባ ሸነን አፍሪካ ፌስቲቫል ለመታደም አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል፡፡በቆይታቸውም ከፌስቲቫሉ በተጨማሪ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡ዛሬ ማለዳ ደግሞ በወዳጅነት ፓርክ በመገኘት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደረጉ ሲሆን፤ በስፍራው ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ የቀድሞው የናይጀሪያ እግር ኳስ ኮከብ ንዋንኩ ካኑ በዚሁ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ እጅግ ውብና የሚያስደንቅ ባህል ያላት ሀገር መሆኗን ተናግሯል፡፡በኢትዮጵያ ቆይታችን የተደረገልን አቀባበልና እንክብካቤ ቤታችን ያለን ያህል እንዲሰማን አድርጓል ያለው የናይጀሪያ የቀድሞ እግር ኳስ ኮከብ፤ በቀጣይም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ እንደሚመጣ ያለውን እምነት ገልጿል፡፡በቆይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ራዕይ መሰረት አድርገው እያከናወኗቸው ያሉ የልማት ስራዎችን ስለመጎብኘታቸውም ተናግሯል፡፡ሌላኛው የናይጀሪያ የቀድሞ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ታሪቦ ዌስት፤ በቆይታቸው የተለያዩ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን መግለፁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

EBC