November 24, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በከባድ ሙቀት ህይወታቸው ያለፈ ሀጃጆች ቁጥር ከ1 ሺህ ተሻገረ

1081 የ10 ሀገራት ዜጎች ህይወታቸው ማለፉ የተነገረ ሲሆን፥ ከ650 በላዩ ግብጻውያን ናቸው ተብሏል

በዘንድሮው ሃጂ የተመዘገበው ጉዳት ከ2015 ወዲህ ከፍተኛው መሆኑ እየተነገረ ነው

በዘንድሮው የሃጂ ጉዞ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከ1 ሺህ መሻገሩ ተነገረ።

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የተለያዩ ሀገራትን ዲፕሎማቶችን ዋቢ አድርጎ ይፋ ባደረገው አሃዝ እስከዛሬ ድረስ 1081 ሃጃጆች ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።

እስካሁን በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት የ10 ሀገራት ዜጎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፥ 658ቱ ግብጻውያን ናቸው።

150 ሺህ ሃጃጆችን የላከችው ፓኪስታን 58 ዜጎቿ ህይወታቸው ማለፉን ይፋ አድርጋለች።

ከ240 ሺህ ኢንዶኔዥያውያን ሃጃጆች መካከልም 183ቱ መሞታቸውን የሀገሪቱ የሃይማኖቶች ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የሱዳን፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዚያ፣ ህንድ፣ ዮርዳኖስ፣ ማሌዥያና ኢራን ዜግነት ያላቸው ሃጃጆችም ህይወታቸው ማለፉን ነው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ያስነበበው።

እስካሁን የገቡበት ያልታወቁ ሃጃጆች ፍለጋ የቀጠለ ሲሆን፥ የሟቾቹ ቀብር መጀመሩም ተጠቁሟል።

ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የውጭ እና ከ300 ሺህ በላይ የሳኡዲ ዜጎች የተሳተፉበት የዘንድሮው ሀጂ በከፍተኛ ሙቀት ተፈትኗል።

የሀገሪቱ የሜዪዮሮሎጂ ማዕከልም በዚህ ሳምንት የመካ ሙቀት 51 ነጥብ 8 ዲግሪ ሴልሺየስ መድረሱን መግለጹ ይታወሳል።

በዚህም እድሜያቸው የገፋና የተለያዩ ህመሞች ያሉባቸው ከ2 ሺህ 700 በላይ ሃጃጆች ሆስፒታል ገብተው እየተካከሙ እንደሚገኙ በትናንትናው እለት ተገልጾ ነበር።

ሳኡዲ በዘንድሮው ሃጂ ህይወታቸው ስላለፈው ሃጃጆች እስካሁን ዝርዝር መረጃ አልሰጠችም።

በየአመቱ ሚሊየኖች በሚሳተፉበትና ከእስልምና አምስት ምሰሶዎች አንዱ በሆነው የሃጂ ስነስርአት መጠኑ ይለያይ እንጂ በየአመቱ ሞት ይደርሳል።

ከስምንት አመት በፊትም በሚና ጠጠር ውርወራ ሲካሄድ በተፈጠረ መረጋገጥ ከ2 ሺህ በላይ ሃጃጆች ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።

Al-Ain

You may have missed