በኢትዮጵያ ለሕጻናት ክትባት ተደራሽነት ፕሮጀክት (ዜሮ ዶዝ) ዘርፈ-ብዙ ፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር 45 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ተደረገ፡፡
በኢትዮጵያ የሕጻናት ክትባት ተደራሽነት ፕሮጀክት (ዜሮ ዶዝ) ዘርፈ-ብዙ ፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ላይ ምክክር ተካሂዷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በመድረኩ ላይ እንዳሉት÷ ፕሮግራሙ በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት በግሎባል የክትባት ኅብረት ኢኒሽዬቲቭ (ጋቪ-ሲፍ) እና ዩኒሴፍ ትብብር ይተገበራል።
ፕሮግራሙ በመላው ሀገሪቱ የሕፃናትን ጤና እና ደኅንነት ለማሻሻል የሚደረገውን ሁሉን አቀፍ ጥረት እንደሚደግፍ አብራርተዋል፡፡
በሚሊየን የሚቆጠሩ ሕጻናት ሕይወት አድን ክትባቶችን እና አስፈላጊ የአመጋገብ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ለክትባት እና የተመጣጠነ ምግብ ፕሮግራም ማስፈጻሚያ እንዲውልም ጋቪ-ሲፍ 30 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን የድርጅቱ የኢትዮጵያ ማኔጀር ኢማኑኤላ ገልጸዋል፡፡
የዩኒሴፍ ተወካይ አቡ ካምፖ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋማቸው ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ 15 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው÷ በሀገሪቱ የሕፃናትን ጤና እና ደኅንነት ለማሻሻል የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ትግበራ በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ክትባት ተደራሽ ያልሆነባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሕጻናት ክትባት እና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በማስቻል የክትባት እና ስርአተ-ምግብ ተደራሽነትን እንደሚያሳድግ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
FBC
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።