November 21, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በመንግስት ለሚገነቡ የህዝብ አግልግሎት ሰጭ ተቋማት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ከማሟላት አንጻር የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ ።

ባሁኑ ሠዓት በሸካ ዞን ማሻ ከተማ ላይ ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የማሻ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህብረተሰብን በማሳተፍ የተቋሙን ግቢ ከማስዋብ አልፎ ለአስተዳደር ስራ የሚያገለግሉ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ሟሟላት እንዲቻል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተደርጓል ።

በውይይቱም ላይ የተገኙት የማሻ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አካሉ ሀልቶ በወቅቱ እንዳሉት በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ሥራው ተቋርጦ የቆየውን የሆስፒታል ግንባታ በፍጥነት አጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግና አስተዳደራዊ ስራዎችን ለማቀላጠፍ ቁሳቁሶችን የሟሟላት ሥራ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል ።

ለዚህ ሥራ ስኬት ከተማ አስተዳሩ የከተማ ነጋዴዎችን በማሳተፍ 3 መቶ ሺ ብር ከመሰብሰብ አልፎ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸው በሆስፒታሉ ግቢ የኤሌክትሪክ ፣የውሃና አጠቃላይ የግቢ መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት ባሻገር ለአስተዳደር ስራዎች የሚሆኑ ተግባራትን ከማከናወን አንጻር የበጀት እጥረት መኖሩን ገልፀው ህብረተሰቡ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል ።

ከሀግፕር ውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ተቀናጅተው በሰሩት ስራ ለህክምና ተግባር የሚውሉ ማሽኖች መግባታቸውን የተናገሩት አቶ አካሉ የክልሉ መንግሥትም 10 ሚልዬን ብር በጀት መድቦ ብሩ እስኪ ፈቀድ ድረስም ለሆስፒታሉ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ለሟሟላት ገቢ የማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የማሻ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሳሙኤል ገቦ በበኩላቸው ሆስፒታሉ በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥበት ለማድረግ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጀቶች ፣ከባለሀብቶች እንዲሁም ከአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ገቢ ለማሰባሰብ አቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል ።

ህብረተሰቡ ሆስፒታሉ ለአከባቢው የሚሰጠውን ጥቅም በመገንዘብና ከተዛቡ እይታዎች በመራቅ የሀይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም አካል የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል ።

የፕሮጀክቱ መሐንድስ አቶ ከለለኝ ቢረዳ ሆስፒታሉ በፍጥነት ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ከዞን አስተዳደር ጨምሮ በየ ደረጃው የሚገኙ አካላት ያደረጉት ድጋፍና ክትትል የሚደነቅ መሆኑን ገልፀው ግንባታው ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ተሰርቶ በቅርብ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለብዙ ዘመናት በሌሎች አካባቢ የሚገኙ ሆስፒታሎች ሄደው በመታከም ለተለያዩ እንግልት እየተዳረጉ መቆየታቸውን በመግለፅ አሁን ላይ ይህ ሆስፒታል በአቅራቢያቸው ተገንብቶ መጠናቀቅ ላይ በመደረሱ መደሰታቸውን በመግለጽ ለዚህም ስኬት ድጋፍና ክትትል ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በፍጥነት ለአገልግሎት መብቃት እንዲችልም የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጭምር ተናግረዋል።

ዘጋቢ አስቻለው አየለ – ከማሻ ቅርንጫፍ

ለተጨማሪ መረጃ ከታች ባሉት ድረ ገጾች ይከታተሉን!

Facebook=https://www.facebook.com/profile.php?id=61552831883490

telegram =https://t.me/MashaFmradio

tiktok=https://www.tiktok.com/@masha_fm103.8?_t=8h8vFNn1ToE&_r=1

YouTube=https://youtube.com/@MashaFM-op5hb?si=4gRo1QtHJYQoGZqY

Instagram=https://instagram.com

You may have missed