October 5, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በዓረብ ሀገራት የሥራ ስምሪት ላይ ህገ-ወጥ ደላሎች አሁንም ዜጎችን ለኪሳራ እየዳረጉ መሆኑ ተመላከተ

 በዓረብ ሀገራት የሥራ ስምሪት ላይ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳትና ኪሳራ ለመከላከል እየተሰራ ቢሆንም ህገ-ወጥ ደላሎች አሁንም አሉታዊ ተጽዕኖ ማድረሳቸው እንዳልቆመ ተገለጸ።

ዜጎች የተሻለ ገቢ ለማግኘት፣ ኑሯቸውን ለማሻሻልና ቤተሰባቸውን ለመደገፍ አልመው ወደ ዓረብ ሀገራት የመሄድ ፍላጎት ያሳያሉ።

ይህንን ፍላጎት በመጠቀም ህገ-ወጥ ደላሎች በነጻ የሚሰጥን የዓረብ ሀገራት የሥራ ስምሪት ዜጎችን በማታለል ያልተገባ ወጪ እንዲያወጡና ለኪሳራ እንዲዳረጉ ብሎም ተስፋ እንዲያጡ እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል።

የእነዚህ ህገ ወጥ ደላሎች ሰለባ ከሆኑት መካከል አለምዘውድ ገብሬ እና ሌሊሴ ከበደ ለአብነት ይጠቀሳሉ።

አለምዘውድ በጀበና ቡና ማፍላት ሥራ ተሰማርታ ከእለት ወጪዋ ቆጥባ ያጠራቀመችውን 70 ሺህ ብር ወደ ዓረብ ሀገር እንልክሻለን ባሏት ህገ ወጥ ደላሎች ተበልታለች።

ገንዘቡን ከከፈለች ከወር ቆይታ በኋላ ቪዛ መጥቶልሻል በሚል ደላሎቹ ወደ አዲስ አበባ ልከዋት በአዲስ አበባ ከምትገኝ ሌላ ሕገ-ወጥ ዳላላ ጋር ያገናኟታል።

በዚህም ያለ ምንም የጤና ምርመራ እና የስራ ብቃት መመዘኛ ሰርተፊኬት በቱሪስት ቪዛ ወደ ቤሩት በ15 ሺህ የኢትዮጵያ ብር የወር ደመወዝ እንደምትሄድ ደላላዋ ትነግራታለች፡፡

በዚህ ጊዜ በመጀመሪያ ደላላ በ35 ሺህ ብር ደመወዝ ወደ ዱባይ እንደምትሄድ የተነገራት አለሚቱ ከደላላዋ ጋር ግጭት ውስጥ ገባች።

ይህን ተከትሎም አለም ዘውድ ቤሩት አልሄድም በሚለው ሃሳቧ በመጽናቷ ደላላዋ የቪዛ እና የቲኬት እንዲሁም ለሌሎች ወጪዎች የወጣ በሚል ከ70 ሺህ ብሩ ተጨማሪ 100 ሺህ ብር ካልከፈልሽ አትሄጅም ትላታለች፡፡

ለተወሰኑ ቀናት ቤቷ አግታ ካቆየቻት በኋላ እንደምንም ጠፍታ የገጠማትን ችግር ከነገረቻቸው ደጋግ ሰዎች ገንዘብ ለምና ወደ ክፍለ ሀገር እንደሄደች ትናገራለች፡፡

ሌላኛዋ ተመሳሳይ ችግር ያጋጠማት ሌሊሴ ከበደ ወደ ዓረብ ሀገር ለመሄድ ያነጋገረችው ሕገ-ወጥ ደላላ ከ50 ሺህ ብር በላይ ተቀብሎ ከሌላ ደላላ ጋር ካገናኛት በኋላ ጉዱዩ ሳይጠናቀቅ አድራሻ ማጥፋቱን ትናገራለች።

በመሰልና በተለያዩ መንገዶች ወደ ዓረብ ሀገራት ሄደው በስራ የተሠማሩ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን በአሰሪዎቻቸው አሰቃቂ እና ዘግናኝ የመብት ጥሰት እንደሚፈጸምባቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አለምዘውድን ካጭበረበሯት ሕገ-ወጥ ደላሎች ጋር ባደረገው ቆይታ፥ ሁሉም ሕገ ወጥ ድርጊቱን መፈጸማቸውን አምነዋል፤ ሒደቱን ለዓመታት ያለምንም ችግር እንደሰሩበትም ይናገራሉ።

በተለይም አዲስ አበባ አለምዘውድን የተቀበለቻት ደላላ አፓርትመንት በመከራየት ሕገ ወጥ ድርጊቱን በስፋት እንደምትሠራ ኤፍ ቢ ሲ በቦታው በመገኘት ተመልክቷል።

ደላሎቹ ያለ አግባብ የተቀበሉትን ገንዘብ እንዲመልሱ ተጠይቀውም ምንም አታመጡም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ይሁንና በዓረብ ሀገራት በሚከናወን የሥራ ስምሪት ሒደት ውስጥ ሕገ-ወጥ ደላሎችን ከሥርዓቱ የሚያስወጣ አዲስ አሰራር መተግበር መጀመሩን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በሚኒስቴሩ የስራ ገበያ መረጃ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ዋለቃ ÷ በዓረብ ሀገራት በሚደረግ የሥራ ስምሪት ሒደት ውስጥ ሕገ ወጥ ደላሎች ከፍተኛ ተግዳሮት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም ከክፍለ ሀገር ወደ ዓረብ ሀገራት መሄድ የሚፈልጉ ሴቶች በቂ መረጃ ስሌላቸው በሕገ-ወጥ ደላሎች መጠነ ሰፊ ችግር እንደሚደርስባቸው አንስተዋል።

የዓረብ ሀገራት የሥራ ስምሪት በነጻ እንደሚሰጥ ገልጸው፥ ደላላዎች ግን የመረጃ ክፍቱን ተጠቅመው ከ60 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር እንደሚያስከፍሉ ጠቁመዋል።

ሕገ-ወጥ ደላላዎችን ከሒደቱ በማስወጣት ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ብዝበዛ ለማስወገድም ሚኒስቴሩ አዲስ አሰራር መተግበር መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ወደ ዓረብ ሀገራት ለስራ መሄድ የሚፈልጉ ዜጎች መጀመሪያ ወደ ኤጀንሲዎች እንደሚሄዱ ጠቅሰው÷ በአዲሱ አሰራር ግን ዜጎች መጀመሪያ ወደ ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የመግባት ግዴታ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

በተቋማቱ የሙያ ምዘና ሰርተፊኬት (ሲኦሲ) ካገኙ በኋላም ሚኒስቴሩ ብቁ የሆኑትን ኤጀንሲዎች ባቀረቡት ፍላጎት መሰረት እንደሚያከፋፍል ተናግረዋል።

ይህም ሕገ ወጥ ደላላዎችን ከሒደቱ ከማስወጣት ባለፈ ሰራተኞች በዓረብ ሀገራት በሥራ ከተሰማሩ በኋላ የመብት ጥሰት እንዳይገጥማቸው ኤጀንሲዎች የሚያደርጉትን ክትትል መቆጣጠር እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።

FBC