ማሻ ፣ የሚያዝያ 20፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የሸካ ዞን ፖሊስ የምርመራ መዝገብ እና የሸካ ዞን ፍትህ መምሪያ ዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው አንደኛ ተከሳሽ ታሪኩ ደምሴ እና ሁለተኛ ተከሳሽ ሰለሞን መላኩ የእስራት ቅጣቱ ሊወሰንባቸው የቻለው የግድያ ወንጀል እና ከባድ የዉንብድና ወንጀል በመፈፀማቸው ነው፡፡
የሸካ ዞን ፖሊስ በምርመራው እንዳረጋገጠው 1ኛ ተከሳሽ ታሪኩ ደምሴ፤ሁለተኛ ተከሳሽ ሰለሞን መላኩ እና ለጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ካልዋለው ግብራበራቸው ጋር በመሆን ጦርና ገጀራ በመያዝ በየኪ ወረዳ ፊዴ ቀበሌ ልዩ ስፍራው ፊዴ ገማ 02 ተብሎ በሚጠራበት አከባቢ ህዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 6:00 ሰዓት የግል ተበዳዮችን መንገድ በመጠበቅ የግድያና የዘረፋ ወንጀል መፈፀማቸውን ፖሊስ አረጋግጧል፡፡
ዐቃቤ ህግ በክስ ዝርዝሩ እንዳመላከተው 1ኛ ተከሳሽ ታሪኩ ደምሴ የግል ተበዳይን በያዘው ገጀራ ጭንቅላቱ ላይ በመቁረጡ ህይወቱ እንዲያልፍ ሲያደርግ፤ለጊዜው ያልተያዘው ተጠርጣሪ ሌላኛውን የግል ተበዳይ በያዘው ጦር መቀመጫው ላይ ወግቶት መሬት ከጣለው በኃላ ከሁለቱ ተጎጂዎች የተለያዬ ንብረቶችና ጥሬ ብር በጥቅሉ 22 ሺህ ብር መውሰዳቸውን በዋና ወንጀል አድራጊነት ሁለቱንም ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
ዐቃቤ ህግ በሁለተኛ ተከሳሽ ሰለሞን መላኩ ሁለቱ ግለሰቦች ጦርና ገጀራ በመያዝ የወንጀል ድርጊቱን ሲፈፅሙ ሁለተኛው ተከሳሽ የወንጀል ድርጊቱን ሰዎች ደርሰው እንዳይከላከሉ መንገድ በመጠበቅ በፈፀመው በዋና ወንጀል አድራጊና ተከፋይ በመሆን በፈፀሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
የሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቴፒ ምድብ ችሎት ከዐቃቤ ህግ የቀረበለት ክስ ግራ ቀኙን ሲያከራክር ቆይቶ ተከሳሾቹ በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ክስ ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ ሁለቱንም ጥፋተኛ ነዉ ሲል የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል።
በዚሁ መሠረት የሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቴፒ ምድብ ችሎት ሚያዚያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት አንደኛ ተከሳሽ ታሪኩ ደምሴ እና ሁለተኛ ተከሳሽ ሰለሞን መላኩ እያንዳንዳቸው በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንድቀጣ ውሳኔ መተላፉን ከሸካ ዞን ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት የደረሰውን መረጃ ጠቅሶ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ዘግቧል፡፡
More Stories
በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሙስናን ለመከላከል በተደረገው ጥረት ከ85 ሚሊዮን በላይ ብር የህዝብ ሃብት ማዳን ተችላል
ኢትዮጵያ እና ኢንግሊዝ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ እና ኢኮኖሚ ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ ተስማሙ
አትሌት ትዕግስት አሰፋ አሸነፈች