April 29, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

መንግስት በፈጠራና ክህሎት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ማሻ ፣ የሚያዝያ 20፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከ ’አፍሪካ ብሬንስ’ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል መካሄድ ጀምሯል።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ ቀጣዩን ትውልድ ለመገንባት ትምህርት፣ ቴክኖሎጂና ክህሎት በጣም ወሳኝ ናቸው ብለዋል፡፡

በዚህ ጉባኤ ትርጉም ያለውና የሚተገበር ውይይት እንደሚደረግ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ትምህርትና ክህሎትን ማዕከል በማድረግ በትምህርት ቤት ግንባታና መሠረተ ልማት ማሻሻል፣ በዲጂታል ኔትዎርክ ግንባታ እንዲሁም በፈጠራና ክህሎት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፤ ታላላቅ ሀገራት ወደ ታላቅነት ማማ የወጡት በተጠናከረ የዜጎች ትምህርት ትከሻ ላይ ነው ብለዋል፡፡

አፍሪካ የወጣት ትውልድ አህጉር ናት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህ ትውልድ ደግሞ ከዓለም ጋር ተስማምቶ እና ተወዳድሮ ለመቀጠል የሚያስችል አቅም የሚሰጥ ስርዓት መዘርጋት ተገቢ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ አሁንም የትምህርት እና የዲጂታላይዜሽን ጉዞን በማሳካት በኩል ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ለነገው ትውልድ የምናደርገውን የትምህርት እና የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት በተቀናጀ እና በተቀላጠፈ መልኩ ማከናወን ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ አፍሪካ በዚህ ረገድ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ እንስራ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ አሁን ያለንበት የዓለም ሁኔታ በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ መጪውን ትውልድና ወጣት በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በክህሎት ማዘጋጀት ይጠበቃል ብለዋል።

በትምህርት፣ በቴኖሎጂና በክህሎት ዘርፍ የሚደርገው ይህ ውይይት በትክክል ለአፍሪካ ለውጥ መሠረት የሚጣልበት ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

በጉባዔው ከትምህርት፣ አይሲቲ እና ክህሎት ጋር የተያያዙ ወሳኝ አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

በጉባኤው የትምህርት፣ የቴክኖሎጂና ክህሎት ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ሀገራት የዘርፉ ሚኒስትሮችና ልዑካን ቡድን አባላት፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የትምህርት አጋር ድርጅቶች፣ የግሉ ሴክተር ኢንቨስተሮች እየተሳተፉ ይገኛል።

ኢቢሲ