ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከመቱ-ማሻ የተገነባው ባለ 230 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ የመብራት መስመር ዝርጋታ ተጠናቆ የመጀመሪያ ዙር መብራት የማብራት ሙከራ ስራ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ዞኑ ቀደም ሲል ዘርፈ ብዙ የልማት ጥያቄዎች የነበሩበት አካባቢ ሲሆን አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልል መንግስት ከተዋቀረ በኋላ የነበሩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ግንባታው ለማሻና አካባቢዋ ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ዞኖችና ክልሎችም ትልቅ ብስራት ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ለሁሉም ማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነው ብለዋል።
ለግንባታው ስኬት የኢሉአባቦር ዞን አስተዳደርና የዞኑ ማህበረሰብ በየደረጃው ያሉ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ድጋፍ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባልና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አዝመራ አንደሞ በመርሃግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የኃይል ማስተላለፊያና የሳብስቴሽን ግንባታው መጠናቀቅ የማሻ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የዘመናት የህዝብ ጥያቄ የነበረና መንግስት የህዝቡን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እየፈታ መምጣቱን አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የተከበሩ አቶ አዝመራ አክለውም አሁን በጅምር ላይ ያሉም ሆነ በቀጣይ ለሚገነቡ ፕሮጀክቶችም መንግስት ልዩ ትኩረት በመስጠት ህብረተሰቡን በማሳተፍ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ዞኑ የበርካታ ሀብቶችና ፀጋዎች ባለቤት በመሆኑ ይህንን ፀጋ ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር ህይወት በሚቀይሩ ተግባራት ማተኮር ይኖርብናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤለክትሪክ ኃይል ምክትል ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አንዷለም ሲዓ ለዘመናት የህዝብ ጥያቄ የነበረው የመብራት ጥያቄ ለዝህ በመብቃቱ ህዝቡ እንኳን ደስ አላችሁ፤ደስ አለን ብለዋል።
ለዚህ መሰረተ ልማት መሳካት በየደረጃው ያሉ የስራ ኃላፊዎችና አመራር ላደረጉት አስተዋፅኦ አመስግነው የታለመለትን አላማ ከግብ እንዲደርስ በሰው ሰራሽ የምመጡትን ችግሮች ለመታደግ በጋራ መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
በማስጀመሪያው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የማሻ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት መንግስት የዞኑ መሰረተ ልማት እንዲፋጠን እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልፀው ቀጣይ በሚገነቡ መሰረተ ልማት ከመንግሥት ጎን እንደሚሆኑም ተናግረዋል።
የመብራት መሰረተ ልማት ለማሻና አካባቢው ነዋሪዎች የዘመናት ጥያቄ የነበረና በቀደሙ የመንግስት መዋቅሮች በተለያዩ ጊዜያት ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ ሳያገኝ ቆይቶ አሁን መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት ምላሽ እያገኘ መምጣቱን ተናግረዋል።
መንግስት መሰረተ ልማቶችን የማስጀመር ብቻ ሳይሆን ሪቫን መቁረጥ መቻሉን ያሳየበት ልዩ ብስራት በዞኑ እየታየ መሆኑን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎች ለዚህም ማሳያ በዞኑ ተመርቀው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የሆስፒታል ፣ የመንገድና የመብራት መሰረተ ልማቶች ማሳያ ናቸው ብለዋል።
የክልሉ መንግስትም ለተጀመሩ መሰረተ ልማቶች ልዩ ትኩረት በመስጠትና የቅርብ ክትትል በማድረግ ተጀምረው እስኪጠናቀቁ ድረስ እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች በመሆኑ ህዝቡም የተጀመሩ ልማቶችን ቁጥጥርና ክትትል ከማድረግ አንፃር ከመንግሥት ጎን ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ በዞኑ እየታየ ያለው መሰረተ ልማት ከፍተኛ ለውጥ እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት የሸካን ህዝብ የዘመናት ጥያቄ ታሪክ የቀየረ መሆኑን ያየንበት ነው ብለዋል።
የመብራት መሰረተ ልማት መጀመሩ አልሚ ባለሀብቶች ለዞኑ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱና የከተማዋም ዕድገት እንዲፋጠን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም ተናግረዋል።
የግንባታውን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴን የዓለም ባንክ በቅርብ ጠንካራ ክትትልና ገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ለዚህ መድረሱን አንስተዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።
በመርሃግብሩ ላይ የፈደራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ኢትዮጵያ ኤለክትሪክ አገልግሎት ኮርፖሬሽን የስራ አስፈፃሚዎችና ባለሙያዎች ፣ የመቱ-ማሻ 130 ፕሮጀክት ማናጀርና ባለድርሻ አካላት ፣ የሸካ ዞን፣የማሻ ወረዳና የማሻ ከተማ የስራ ኃላፊዎች ፣ባለሙያዎችና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል::
More Stories
የለውጥ ዓመታቱ በፖለቲካ ምህዳራችን አካታችነትና አቃፊነት የተረጋገጠበት ነው- አደም ፋራህ
የሸካ ንጉስ ቴቺ ቄጃቺና የምክራቾ አባላት በማሻ ወረዳ ከሚገኙ የጎሳ መሪዎች ጋር ዉይይት አካሄዷል።
ኢ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን “አዲስ ምዕራፍ” ፕሮግራም ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወሰደ