April 3, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የሸካ ንጉስ ቴቺ ቄጃቺና የምክራቾ አባላት በማሻ ወረዳ ከሚገኙ የጎሳ መሪዎች ጋር ዉይይት አካሄዷል።

ማሻ ፣ የመጋቢት 23፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የዉይይቱ ዓላማ ነባር የጎሳ መሪዎችን በለማፅናትና አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የጎሳ መሪዎችን ለመሙላት እንደሆነም ተጠቁሟል።

ዉይይቱን በባህላዊ  ምርቃት ያስጀመሩት ንጉስ ቴቺ ቄጆቺ በተሰማራንበት ሁሉ መልካም ተግባራትን በማከናወን ህዝባችንን ማሳረፍ ይጠበቅብናል ብለዋል።

በሁሉም ቦታዎች የሚገኙ የጎሳ መሪዎች በእዉነት፣በፍትሐዊነትና በእኩልነት ህዝብን በማገልገል ሠላምን በማፅናትና የሀገርን ልማት በመደገፍ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ተግባራዊ እንዲሆን የተላለፈውን ቲሞና ሼሮ እስከታች በማዉረድ ውጤታማ ለውጥ ማስመዝገብ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል ።

በመድረኩ የተገኙት የማሻ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መስፍን አዳሾ በበኩላቸው በንጉስ ቴቺ ቄጆቺና የምክራቾ አባላት እየተሰሩ ያሉት ስራዎች የሚመሰገን መሆኑን ገልፀው በቀጣይ የጎሳ መሪዎችን እስከ ታችኛዉ መዋቅር በማጠናከር፡በባህልና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እንዲሁም በሠላምና ፀጥታ በጋራ በመስራት የአከባቢዉን ልማት ከዳር ማድረስ አለብን ብለዋል ።

የምክራቾ አባላትም ባህላዊ አስዳደሩን እስከ ታች ድረስ ለማፅናት በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልፀዉ ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ሁላችንም ኃላፍነታችንን በተገቢዉ መወጣት አለብን ብለዋል።

ካተራሻ ካፍሽ ገነ አቾቺ በበኩላቸዉ በባህላዊ አስተዳደር በርካታ ስራዎች መከናወናቸዉን አብራርተው የጎሳ መሪዎችን በመደገፍ ተግባራዊ እንዲሆን የተላለፉ ቲሞና ሼሮ ተፈፃሚ እንድሆኑ ማድረግ አለብን ብለዋል ።

አመፅ፣መካካድና ጥላቻን በማስቀረት የህዝባችን ሠላም በማፅናት አንድነትና መደጋገፍን ለማምጣት የበለጠ መስራት አለብን በማለት ንጉስ ቴቺ ቄጆቺ ለውይይቱ ተሳታፊዎች መልዕክት አስተላልፈዋል ።

ይህን ለማሳካት ፍትሐዊ የዳኝነት ስርዓት በመዘርጋት ቲሞና ሼሮን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል።

ባህላዊ አስተዳደሩ ከመንግስት መዋቅሮች ጋር  በመተባበር በሠላምና በልማት ዙርያ እንዲሰራም ንጉስ ቴቺ ቄጆቺ አስገንዝቧል ።