ማሻ ፣ የመጋቢት 14፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም ) የተፋሰስ ልማት ስራ ከአካባቢ ሥነ-ምህዳር ጥበቃ ባሻገር ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማስቻሉን ኢዜአ ያነጋገራቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አርሶ አደሮች ገለጹ።
በተያዘው ዓመት በክልሉ አንድ ሚሊዮን ዜጎችን በማሣተፍ 213 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ መከናወኑ ተጠቅሷል።
በክልሉ የካፋ ዞን አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ የተራቆቱ አካባቢዎችን ከማልማት ባለፈ ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨመር አስችሏል።
አርሶ አደር ዘውዲቱ ዬቦ እንዳሉት በተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ የተራቆተ ማሳቸው በማገገሙ በቡና፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እና በንብ ማነብ ልማት ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል።
ይህም ከሥነ-ምህዳር ጥበቃ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጠ ስለመሆኑ ነው ያነሱት።
አርሶ አደር ተስፋዬ አበበ በበኩላቸው የተፋሰስ ልማት ምንጮች እንዲጎለብቱ በማስቻሉ በእንስሳት መኖ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አግዛቸዋል።
የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል የካልም ፕሮጀክት አስተባባሪ ሄኖክ ጸጋዬ እንዳሉት ማዕከሉ አርሶ አደሮች በለሙ ተፋሰሶች ላይ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማልማት እንዲጠቀሙ ድጋፍ እየተደረገ ነው።
በተጨማሪም ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን እና የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ማዕከሉ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ያለውን ሥራ ወደ ሌሎች ዞኖች በማስፋፋት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ውብሸት ዘነበ በተያዘው በጀት ዓመት የተፋሰስ ልማት ሥራ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች መሣተፋቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ከ213 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ መከናወኑንም መናገራቸውን የኢዜአ መረጃ ያመለክታል።
በበጋው ወራት የተፋሰስ ልማት ስራ የተሰራባቸው ቦታዎች ላይ በመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ ስራዎችን ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ክልል ኮሚኒኬሽን
More Stories
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ እንዲጠናከር ጥሪ ቀረበ
ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ልዩ የአዳር ትምህርት ተመቻችቶ የመማር ማስተማር ስራ መጀመሩ የበለጠ ውጤት እንድናስመዘግብ አግዞናል ሲሉ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ልዩ የአዳር ትምህርት እድል ያገኙ ተማሪዎች ገለፁ ።
የመጋቢት 24 ፍሬዎች በሁሉም የኢትዮጵያ መንደሮች እንዲዳረሱ ተግተን እንሰራለን – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ