April 3, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በሸካ ዞን እስካሁን የተከናወኑ የፓርቲ እና የመንግስት ስራዎች አፈፃፀምን በሚመለከት ለክልሉ ድጋፍና ክትትል ቡድን ገለፃ ተደረገላቸው

ማሻ ፣ የመጋቢት 08፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም ) በቀጣይ በዞኑ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያም የክልሉ ድጋፍና ክትትል ቡድን እቅድ ቀርቦ የስራ አቅጣጫም አስቀምጧል።

ድጋፍና ክትትል ቡድኑ በተመረጡ መዋቅሮች ምልከታ የሚያደርግ ሲሆን ተግባራት መሬት ላይ በተጨባጭ መኖራቸውን ለማረጋገጥ እና የታዩ ክፍተቶችን በፍጥነት ለማረም ብሎም ምርጥ ተሞክሮ ወደ ሌሎች እንዲሰፋ እንደሚያደርግም ተጠቁሟል።

በሸካ ዞን በ2017 በጀት ዓመት በዋና ዋና ዘርፎች የእስካሁን አፈፃፀም ሪፖርት በብልፅግና ፓርቲ ሸካ ዞን ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ እና የዞኑ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ አለሙ ቀርቧል።

የፓርቲ ስራዎች፣ የኢኮኖሚ እና መሠረተ ልማት፣ የማህበራዊ ልማት እንዲሁም በአስተዳደር ዘርፍ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን በዝርዝር አቅርበዋል አቶ አለማየሁ አለሙ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ተሰማ በመድረኩ እንደገለፁት የፓርቲ እና የመንግስት ሥራዎች አፈፃፀም ምልከታ እንደሚደረግ ጠቁመው ከአፈፃፀም ሪፖርት ጋር ተግባራት በተጨባጭ መሬት ላይ መኖራቸውን ማረጋገጥ ብሎም የታዩ ክፍተቶችን በፍጥነት ለማረም እና ምርጥ ተሞክሮ ወደ ሌሎች እንዲሰፋ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል ።

የገጠር ኮሪደር ልማት ስራን እንደ ሀገር በተያዙ ከልማት እንሼቲቦች ጋር በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ዕድገት ልያመጡ እና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ አመራሩና አባሉ በቁጭት ሊሰራ እንደሚገባም በአጽንኦት አንስተዋል።

በዞኑ ባሉ ሁለት ወረዳዎች እና አንድ ከተማ አስተዳደር እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራት ጉብኝት እንደሚደረግ የጠቆሙት አቶ በላይ እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠልና ጉድለቶችን ለይቶ ለቀጣይ ተግባራት ስኬት መፍትሔ ማበጀት የምልከታው ዓላማ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

የድጋፍና ክትትል ቡድኑ በዋናነት የተከናወኑ ተግባራትን ከመጎብኘት አንፃር ሊታዩ የሚገባቸው ዋና ዋና ቦታዎችን ጥቆማ ያደረጉ ሲሆን ከጉብኝት በኋላ ውይይት የሚደረግ መሆኑን አክለዋል።

በመጨረሻም የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታመነ በቀለ የገጠር ኮሪደር ልማት መተግበሪያ ዕቅድ በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን የገጠር ኮሪደር ልማት በገጠር አካባቢዎች የኢኮኖሚና የልማት ዕድገትን ለማፋጠን እንደሆነ ገልፀው ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያግዝ በመሆኑ በዞኑ የገጠር ኮሪደር ልማት ስራን መተግበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የድጋፍና ክትትል ቡድኑ በሸካ ዞን በ2017 በጀት ዓመት በዋና ዋና ዘርፎች የእስካሁኑን አፈፃፀም ሪፖርት ያዳመጠ ሲሆን የመስክ ምልከታ እንደሚያደርግም ከወጣው መርሃግብር ለማወቅ ተችሏል ።

በመድረኩ የዞኑ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት እና የሴክተር መስሪያ ቤት አስፈፃሚ አካላት ተገኝተዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።