በእግር ኳስ ብዙ ኮሜንታተሮች ተመልክተናል፣ ብዙዎችንም ሰምተናል፤ በብዙዎች ዘንድ የሚወደደው ፒተር ድሩሪ ግን ልዩ ነው። ለዚህ ምስክሮች ደግሞ በጨዋታ ወቅት የሚጠቀማቸው ቃላቶችና አገላለጾች ናቸው።
በህይወት ጉዞ ላይ ብዙ ነገሮች አይነጣጠሉም፤ ደስታና ሀዘን፣ ማግኘትና ማጣት፣ መታመምና መዳን፣ መኖርና መሞት፤ በስፖርቱ ዘርፍ ደግሞ እግር ኳስ እና ፒተር ድሩሪ የማይለያዩ እስኪመስሉ ተጣምረዋል።
በፈረንጆቹ 1967 በእንግሊዝ ዊትሀም ተብላ በምትጠራ ከተማ ተወለደ። አብዛኛውን የኢኮኖሚ ምንጯን በኢንዱስትሪ ላይ በማድረግ ገቢ የምታገኘው ይህች ከተማ÷ ለእግር ኳስ ኢንዱስትሪ ደግሞ ፒተር ድሩሪን ማበርከት ቻለች።
በፈረንጆቹ 1990 በቢቢሲ ሬዲዮ የኮሜንታተርነት ህይወትን የጀመረው ፒተር ድሩሪ÷ በቀድሞ ስሙ የመጀመሪያ ዲቪዚዮን የእግር ኳስ ሊግ (the football league first division) እየተባለ የሚጠራውን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በኮሜንታተርነት በመተንተን ጀምሮ፣ ከዛም በተወዳጆቹ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ዓለም ዋንጫ ላይ በውብ ቃላቶቹ ምስል ከሳች አገላለጾቹ ተመልካችን ሲያስደስት ቆይቷል።
በተለይም በፈረንጆቹ 2010 በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰናዳው በደቡብ አፍሪካው የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ ላይ አዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ በሜክሲኮ ብሔራዊ ቡድን ላይ በሸበላላ አማካኝነት ግብ ስታስቆጥር የፒተር ዱሩሪ ውብ ኮሜንታተርነት ከደስታ መግለጫው ጋር ተዳምሮ በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ሁሌም የማይረሳ ትውስታን ትቶ አልፏል።
ፒተር ዱሩሪ እግር ኳስን በእነዛ ውብ ቃላቶቹ ሳይሰስት ለተመልካች የሚያደርስ፤ እግር ኳስ ካሳየችን ኮሜንታተሮች አንዱና ዋነኛው ነው። “ስለኮሜንታተርነት ሳስብ ሁሌም አንድ ሀሳብ ወደ አዕምሮዬ ይመጣል እሱም እግር ኳስን መውደድ እና የወደድኩትን ነገር እንዴት በጥሩ ቃላት መግለፅ እንደምችል አስባለሁ” በማለትም ይናገራል።
በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር የ2021/22 ውድድር ዓመት ማንቼስተር ዩናይትድ የቀድሞውን ኮከብ ተጨዋቹን ክሪስቲያኖ ሮናልዶን ዳግም ወደ ኦልድትራፎርድ ማምጣት ቻለ። ሮናልዶ በድጋሚ ለማንቼስተር ዩናይትድ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር ሲያደርግ በተንታኝነት የነበረው ፒተር ዱሩሪ “ሮናልዶ ነው፤ ወደ ሜዳ እየገባ ነው። ማዴራ፣ ማንቼስተር፣ ማድሪድ፣ ቱሪን እንደገና ማንቼስተር፤ በቀዩ ማለያ ደምቋል፣ ወደ ተወዳጁ ሊግም ተመልሷል። እያደር እንደ ወይን የሚጣፍጥ አቻ የማይገኝለት፤ ወደ ቀድሞው ክለቡ በድጋሚ ተመልሷል፣” በማለት በእነዛ ውብ ቃላቶቹ ፖርቹጋላዊውን ተጨዋች ገልጾታል።
በተንታኝነት ዘመኑ ብዙ ጨዋታዎችን መምራት ችሏል፤ ከእነዚህም ውስጥ በፈረንጆቹ 2018 የሩሲያ የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ክሮሺያ እና ፈረንሳይ ያደረጉትን ጨዋታ የተነተነ ሲሆን÷ በኳታሩ ዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ፈረንሳይ ከአርጀንቲና ያደረጉትንም ጨዋታ በተንታኝነት መምራት ችሏል።
የእግር ኳስ አፍቃርያን ይህን እንግሊዛዊ የእግር ኳስ ኮሜንታተር ቁጥሮችን ከጨዋታዎች ጋር አንድ ላይ በማዋሀድ በአዕምሮ ውስጥ መቼም እንዳይረሳ ማድረግ የሚችል የኮሜንታተር ንጉስ ነው ይሉታል። የእሱ ድምፅ በጨዋታዎች መሀል ካለ ሁሌም እግር ኳስ ይደምቃል። ህይወት ቆማ አትጠብቅም፡፡ የሰው ልጅም ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል ታዲያ ይህ የእግር ኳስ አቀንቃኝ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በውብ ቃላቶቹ ለተመልካች ሲያስተላልፍ ቆይቶ፤ አንድ ቀን ከኮሜንታተርነቱ ራሱን ያገላል፡፡ እግር ኳስ ፒተር ዱሩሪ ይጎድልባታል፡፡ ያኔ እግር ኳስ እና የእግር ኳስ አፍቃርያን ምን ይሰማቸው ይሆን? ወደ ፊት ጊዜ የሚመልሰው ይሆናል።
More Stories
በማሻ ወረዳ በህል ቱሪዝምና ስፖርት ጽ/ቤት አዘጋጅነት ለተከታታይ 5ቀን ስካሄድ የነበረው የእግርኳስ ውድድር ፍጻሜውን አግኝተዋል።
የዋልያዎቹ ድል ለቀጣይ ጨዋታ አቅም ይሆነናል – አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ
ኢትዮጵያ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከዓለም 3ኛ በመሆን አጠናቀቀች