April 3, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኢትዮጵያ ቡና ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል

ማሻ ፣ የመጋቢት 08፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም ) የኢትዮጵያ ቡና ቻይናን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ደዋኖ ከድር ገለጹ።

በቤጂንግ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሶስተኛዉ “Beijing CBD International Coffee Culture Festival” ላይ ተሳትፎ አድርጓል፡፡

ፕሮግራሙ የተካሄደው ”The World’s Coffee Heritage-The Light of Ethiopia-The Cradle of Coffee Culture” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

በቻይና የንግድ ሚኒስቴር የሰሪኩሌሽን ኢንዱስትሪ ፕሮሞሽን እና የኢትዮጵያ ሚሲዮን ሁነቱን በጋራ አዘጋጅተውታል።

በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ደዋኖ ከድር የኢትዮጵን ቡና አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸውም ኢትዮጵያ የጥሩ ጣዕም(አረቢካ) ቡና መገኛ፣ ጥራት ያለው ቡና አምራች እና ላኪ እንዲሁም የጥሩ ጣዕም እና የተለያዩ ባህሪያት ያላቸዉ በርካታ የቡና ዝርያዎች ባለቤት ናት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ፍላጎት የቻይና ገበያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪም በመንግስት በኩል የቡናን አመራረት እና ጥራት ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

መንግስት በሰጠው ትኩረት በኢትዮጵያ የቡና ምርት በብዛት እና በጥራት እያደገ መምጣቱንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ከቻይና ኩባንያዎች ጋር በቡና ወጪ ንግድ እና በሌሎች የቡና ዘርፎች ላይ በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ለዚህም ሚሲዮኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው አምባሳደሩ የገለጹት።

በፌስቲቫሉ የተለያዩ የኢትዮጵያ የቡና ወጪ ምርቶች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን በቡና ንግድ ዙሪያ ከተለያዩ ኩባንያ ተወካዮች ጋር ውይይቶች ተደርጓል።

በፕሮግራሙ ላይ ኩባንያዎች፣ የተለያዩ ቡና ገዢዎች፣ ላኪዎች፣ አከፋፋዮች፣ አቀነባሪዎች እና በቡና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የመንግስት እና የግል ተቋማት መሳተፋቸውን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

ኢፕድ