March 14, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት

ማሻ ፣ የመጋቢት 03 ፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም ) የሐረር አቅጣጫና ተስፋ በሐረር ከተማ የተጀመረውን የኮሪደር ልማትና አካባቢውን ለኑሮና ለቱሪዝም ምቹ የማድረግ እንቅስቃሴ ተመልክቻለሁ። በከተማዋ የተጀመረው ሥራ ዕምቅ ዐቅምን ማወቅ፤ አካባቢያዊ ጸጋዎችን ለብልጽግና መጠቀም፤ ማኅበረሰብን ማስተባበር እና የአመራር ቁርጠኝነት ሲደመሩ – ለውጥ እንዴት እንደሚመጣ ማሳያ ነው።

ሐረርን እንደ ተምሳሌት በመውሰድ አካባቢዎቻችን ለመቀየር የሚያስችሉ ሰባት ልምዶች እና አቅጣጫዎች ቀጥለው ቀርበዋል።

1. የአመራር ቁርጠኝነት፦ ሐረርን በዋናነት የቀየራት የአመራር ቁርጠኝነት ነው። ዓመታዊ ገቢያቸው ከሌሎች ያነሰ ነው። ለሥራው ያዋሉት በጀትም ዝቅተኛ ነው።

ቀሪውን ያሟሉት አመራሩ ቁርጠኛ ሆኖ ቀን ከሌት በመሥራት እና ዐቅሙን አሟጥጦ በመጠቀም ነው። ሌሎች ከዚህ መማር አለብን።

2. ታሪካዊ ሀብትን ዐውቆ ማልማት፦ ሐረር እና አካባቢዋ ከሺ ዓመታት የዘለለ ታሪካዊ ሀብት አላቸው። ይሄንን ሀብት በማወቅ እና በመለየት ለጉብኝት ምቹ አድርገውታል። መንገድ ተሠርቷል፤ ሙዝየም ተገንብቷል። የአካባቢውን ንጽሕና የመጠበቅ ሥራም እየተሠራ ነው። ይሄ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው።

3. ጥንታዊ አካባቢን አናብቦ ማዘመን፦ የሺ እና የመቶ ዓመታት ታሪክ ያላቸው የኢትዮጵያ ከተሞች እንዴት መቀየር እንዳለባቸው ሐረር ተምሳሌት ናት። ጀጎል ተለውጧል። የውስጥ ለውስጥ መንገዱ ተዘርግቷል። ግንቡን ለመጠገን የተሠራው ሥራ፣ የመብራት ሥራው፤ ጥንታዊው ከተማ የወዳደቁ ቤቶች መከማቻ እንዳይሆን እየተሠራ ያለው ሥራ፣ ጀጎልን ሁሌ አዲስ እንድትሆን አድርጓታል። ያረጁና ያፈጁ ከተሞች እንዴት እንደሚቀየሩ መማሪያ ነው።

4. አካባቢያዊ ልዩ ጸጋን ለቱሪዝም መጠቀም፦ ሐረር ሰዎችና የዱር እንስሳት ተግባብተው የሚኖሩባት ከተማ ናት። ለዚህ አንዱ ማሳያ የጅብ ትርዒት ነው። ከመቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ ሐረርን የጎበኙ ጸሐፍት ይሄንን ትርዒት አድንቀው ጽፈዋል። ይሄንን ትርዒት ወደ ዘመናዊ የቱሪስት መዳረሻነት ለመቀየር በመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ መነሻነት የጅብ ትርዒት ማሳያ አምፊ ቴአትር በሐረር ተገንብቷል። በየአካባቢያችን ያሉትን ልዩ ጸጋዎች በዚህ መንገድ ነው ዐውቀን ማልማት ያለብን።

5. ለኮሪደር ሥራ አካባቢያዊ ዕውቀትን መጠቀማቸው፦ በአንዳንድ ከተሞች የኮሪደር ልማት በውድ ዋጋ የሚገኙትን የመንገድ መብራቶች ሐረሮች በአካባቢያቸው በማምረት በርካሽ አግኝተዋቸዋል። የመንገድ መብራትን ለመጠገን ያለውን ችግር በሚፈታ መልኩ ሐረሮች የመንገዶቻቸውን መብራቶች በርካሽና በተሻለ መንገድ ሠርተዋል። ሥራን ውድ የሚያደርገው ሀብትን እና ዕውቀትን በሚገባ አለመጠቀም ነው።

6. በአካባቢ ጸጋ አካባቢን ማስዋብ፦ ሐረር ላይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የተሠሩት በሐረር ድንጋይ ተጠርበው ነው። ይሄ ተግባር አዱሱ ግንባታ ከነባሩ ጋር እንዲጣጣም አድርጓል። ለአካባቢው ወጣቶችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ በጥቂት ወጪ ብዙ ሥራ ለመሥራትም አስችሏል፤ የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር አድርጓል። ዘወር ዘወር ብለን መሬቱን እንየው። ለልማት የሚውል ብዙ ሀብት አለው።

7. አስፍቶ ማሰብ፦ ሐረር በቆዳ ስፋት ከብዙ ክልሎች ያነሰች ናት። ታሪካዊ ከተማ በመሆኗም የነዋሪዎች መጨናነቅ እና የቦታ ጥበት አለ። ጠባብን ቦታን የሚያሰፋው ሰፊ አመለካከት ነው። ሩቅን የሚያቀርበው አርቆ ተመልካችነት ነው። የሐረር የኮሪደር ልማት ሰፊ የሆነው በዚህ ዕይታ ነው። በዚህ ዕይታ የተሠሩት የእግረኛ መንገዶች፣ ፓርኮች፣ አምፊ ቴአትሮች፣ አረንጓዴ ሥፍራዎች፣ ወዘተ. አስደናቂ ናቸው። አስፍቶ ማሰብ ጥቁቱን ያበዛል፣ ሩቁን ያቀርባል።

እነዚህ ሁሉ ሥራዎች ሀብት እንዲያመነጩ ምቹ ሆቴሎች ያስፈልጋሉ። ኢንቨስተሮችን ስቦና አበረታትቶ ንግዱን ማቀላጠፍ ይገባል።

በከተማ የተሠሩ ሥራዎች ዘላቂ እንዲሆኑ በገጠሩ የሌማት ትሩፋት ይበልጥ መስፋፋት አለበት። ዘመናዊ ግብርናና የግብርና ተዋጽዖ ማቀነባበሪያዎች እንዲፈጠሩ እንትጋ። የአካባቢያችንን ገበያዎች እናነቃቃቸው።

ከዚህ ጎን ለጎን የሕዝቡን የመለወጥ ፍላጎት፣ የሰላም ፍላጎት እና ታታሪነት እንደ ሀብት በመውሰድ ሕዝብ የሚያረካ አገልግሎት እንስጥ።

ሐረሮች በርቱ። ግን ገና ብዙ ይቀረናልና ረክታችሁ እንዳትቆሙ። ሕዝብን እያወያያችሁና እያስተባበራችሁ ሐረርን ከዓለም ጋር ለማወዳደር እስክትችሉ ትጉ።

ፋና