February 19, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ከኢፌዲሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ

ሃገራችን ኢትዮጵያ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ የሚካሄደውን የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ከወትሮው በላቀ መልኩ በድምቀት ለማስተናገድ አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ እንግዶቿን ለመቀበል ዝግጁ ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት (ወይም በቀድሞ አጠራሩ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) ምስረታም ሆነ ከተመሰረተ በኋላ ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ጋር በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች:: የጎብረቱ መቀመጫ እንደመሆናችንም በየዓመቱ የሚካሄዱ የአስፈጻሚዎች እና የመሪዎች ስብሰባዎችን በድምቀት ስናስተናግድ ቆይተናል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ሃገራችን ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም ማቆጥቆጥና መለምለም የተወጣችውን ሚና የሚዘክር ቋሚ ሃውልታችን ነው:: ከዚህም ባሻገር ሌሎች አፍሪካውያን ወንድም እህቶቻችን ለሃገራችን ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ስኬት የዋሉትን ውለታ የሚዘክርና በተለይም በተቸገርንባቸው ጊዜያት ሁሉ አፍሪካውያን ወገኖቻችን ያደረጉልንን ድጋፍና አለሁ ባይነት የሚያሳይ ነው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማዕከል እንድትሆን ከሚያደርጓት በርካታ ምክንያቶች አንዱ የአፍሪካ ኅብረት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ መሆኗ ነው:: መዲናችን አዲስ አበባ ከኒው ዮርክእና ጄኔቫ በመቀጠል የበርካታ ዲፕሎማሲያዊ ተቋማት መገኛ ናት:: ይህ የዲፕሎማሲያዊ ማዕከልነታችን ላይ የምንኮራብትና ሰንደቅ ዓላማችን በኩራት የሚያውለበልበው የኢትዮጵያ አየርመንገድ ሲጨመርበት አብዛኛው አፍሪካዊ ቢያንስ አንድ ጊዜ ኢትዮጵያን የማየት እድል እንዲያገኝ አድርገዋል፡

በያዝነው ሳምንት ለ46ኛ ጊዜ የሚካሄደው የአስፈጻሚዎች መደበኛ ስብሰባ እና ለ38ኛ ጊዜ የሚከናወነው የመሪዎች ጉባዔ አወትሮው በላቀ መልኩ በርካታ እንግዶች የሚገኙበት ነው። በጉባዔው ርዕስ ብሄሮች ወይም ርዕስ መንግስታት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች እና የልዑካን መሪዎች ተጋባዥ እንግዶችን እና የልዑካን አባላትን ጨምሮ ከ15ሺህ በላይ እንግዶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህንን ጉባዔ ለመዘገብም ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ጋዜጠኞች የመዘገቢያ ፈቃድ ወስደዋል፡፡ ይህንን ኸነት በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን የተቋማትን ቅንጅትና መናበብ በሚያረጋግጥ መልክ 35 የፌደራል ተቋማት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ያሉበት ዐብይ ኮሚቴ እና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው በየጊዜው በመገምገግም ስራውን በውጤታማነት መርተዋል፤ በሦስት ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ብቁ የሆኑ ካዴቶች ሰልጥነው ከነባር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲፕሎማቶች ጋር ተሰማርተዋል፡፡

ከቪዛ፣ ከስተምስ ክሊራንስ እና የሚዲያ ፈቃድ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች በተፋጠነና በተናበበ መልኩ እንዲሰጡ በልዩ ትኩረት ተሰርቷል፤

ሆቴሎች ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ አጋጣሚውን በመጠቀም የሃገራችንን የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲያስተዋውቁ የሚያስችል ደረጃቸውን የጠበቁ መረጃዎች በሦስት ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች (እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ እና አረብኛ) ቀርበዋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የታክሲ አሽከርካሪዎች የመልካም መስተንግዶ ስልጠና ከመውሰድም በተጨማሪ ለእንግዶች የሚያጋሩት መረጃ እንዲታጠቁ ተደርጓል፡፡

እንደ መብራት እና ቴሌኮሚኒኬሽን ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በላቀ ዝግጁነት አገልግሎት እንዲያቀርቡ የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛሉ፡፡

በተለይም ጉባዔው በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታና ደህንነት ግብረ ኃይሉ በቴክኖሎጂ፣ በአሰራር እና በሰው ኃይል ስምሪት ከሌላው ጊዜ በላቀ መልኩ ዝግጁ ሆኗል፡፡

እንግዶቻችን በሚኖራቸው ቆይታ ከስብሰባውም በተጨማሪ በሃገራችን ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ፣ የልማት ጥረቶችንና ውጤቶችን ተዟዙረው እንዲያዩ፣ የኢትዮጵያን ምርቶች እንዲቋደሱና እንዲገበያዩ ለማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት በርካታ ጥረቶች ይጠበቃሉ፡፡

እንደሚታወቀው እንግዶች ወደ ሃገራችን ሲመጡ ከአውሮፕላን ውስጥ አስተናጋጆች ጀምሮ አየርማረፊያ የሚያገኟቸው የተለያዩ ተቋማት አስተናባሪዎች፤ የታክሲ አሽከርካሪና የሆቴል አስተናጋጆችን ጨምሮ ከውስን ሰዎች ጋር ነው መስተጋብር የሚፈጥሩት፡፡ ከእነዚህ ውስን ሰዎች ጋር የሚኖራቸው መስተጋብር ግን ስለኢትዮጵያም ሆነ ስለኢትዮጵያውያን ለረጅም ጊዜ የሚቆይትውስታ የሚጥልባቸው ነው። በመሆኑም እንግዶችን ተቀብለን በምናስተናግድበት ወቅት እንደሙያ ዘርፋችን ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ እንግዳ ተቀባይ ኢትዮጵያዊ እንዲሆን የአደራ ጥሪውን ያስተላልፋል።

እስከ ጉባዔው ፍጻሜ ድረስ በሚኖሩት ቀናት ከመንገድ መዘጋጋት ጋር ተያይዞ የሚኖሩ መጠነኛ መስተጓጎሎችን ሃገራችን ይህን ከፍተኛ ትርጉም ያለው አህጉራዊ ኹነት በማስተናገዷ ከምናገኘው ጥቅም አንጻር በማየት በተለመደው እንግዳ ተቀባይነታችን እንድናስተናግድ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የቀን ውሏችንን ከመርሃ ግብሩ ጋር ለማስናኘት ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት እንድታደርጉ እያሳሰብን፣ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የሚሰጡ መረጃዎችን በቅርበት እንድትከታተሉ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡

በመጨረሻም ይህ ቅድመ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሌት ተቀን ለሰሩ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማት የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት የላቀ ምስጋናውን ያቀርባል።