February 23, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

26 ጎማዎች ያሉት የዓለማችን ረዥሙ መኪና

26 ጎማዎች ያሉት እና 75 ሰዎችን መጫን የሚችል በዓለማችን ረዥሙ መኪና ነው። መኪናው የተሰራው ከስድስት የ1976 ሞዴል ከሆኑ ካዲላክ ኤል ዶራዶ ሊሞዚን መኪኖች ሲሆነብ “ዘ አሜሪካን ድሪም” ይሰኛል።

ከ30 ሜትር በላይ የሚረዝመው ይህ መኪና ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው እ.ኤ.አ በ1986 ሲሆን በሁለት የቪ ኤይት ሞተሮች የተሰራ እና 18 ነጥብ 28 ሜትር ርዝመት ያለው ነበር። በኋላም የዚህ መኪና ሰሪ የሆነው ጄይ ኦህርበርግ መኪናውን በማሻሻል ወደ 30 ነጥብ 5 ሜትር ከፍ አደረገው።

የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብም በፈረንጆቹ 1986 ይህን ግዙፍ ሊሞዚን የዓለማችን ረዥሙ መኪና አድርጎ መዘገበው።

በወቅቱም መኪናው በብዙ መጽሔቶች፣ በቴሌቪዢን ላይ እንዲሁም በፊልሞች ውስጥ ይታይ የነበር ቢሆንም በድንገት ዝናው ጠፍቶ በኒው ጀርሲ ውስጥ ባለ የእቃ ማከማቻ ጀርባ ተጣለ።

ነገር ግን ዛሬ ላይ ሁለት የተሽከርካሪ ፍቅር ያለባቸው ሰዎች ይህን መኪና ከተጣለበት አንስተው አሁን ላይ ያለው መልክ እንዲኖረው እና በድጋሚ የሰዎችን ቀልብ እንዲስብ አደረጉት። 26 አዳዲስ ጎማዎችም የተጨመሩለት ሲሆን ነጭ ቀለምም ተቀብቷል።

ይህ የዓለማችን ረዥሙ መኪና ለየት የሚያደርገው ቁመቱ ብቻ አይደለም። በውስጡ የመዋኛ ገንዳ፣ የመታጠቢያ ገንዳ፣ አነስተኛ የጎልፍ ሜዳ እንዲሁም ትንሽ ሄሊኮፕተር ማሳረፍ የሚያስችል ማኮብኮቢያ ያለው መሆኑ ነው።

ይህን መኪና መንዳት የሚቻለውም በቀጥተኛ መንገድ ላይ ብቻ መሆኑን የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ አመላክቷል። ምክንያቱም ይህን ያህል ርዝመት ያለውን መኪና በመንገዶች ላይ ማዞር ከባድ በመሆኑ ነው ተብሏል።

ስለዚህም ሰዎች ይህ መኪና ለመመልከት ወደ ተቀመጠበት ፍሎሪዳ፣ ኦርላንዶ ውስጥ ባለው ዴዘርላንድ ፓርክ ኦቶ ሙዚየም ጠጋ ማለት እንደሚያስፈልግም በመረጃው ተጠቅሷል።