February 23, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በደም እጦት ምክንያት ሰው መሞት የለበትም በሚል አላማ የሚሰራዉ የደም ባንክ አሁንም ህብረተሰቡ አላማቸውን በመረዳት ደም እንድለግስ ጥሪ አቀረበ።

የመቱ ደም ባንክ በሸካ ዞን ማሻ ከተማ ከበጎ ፍቃደኛ የህብረተሰብ ክፍሎች የሰዉን ህይወት ለማዳን ደም እየሰበሰበ ይገኛል።

የመቱ ደም ባንክ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ወንድሙ ተቋሙ አንድም ሰዉ በደም እጦት ምክንያት መሞት የለበትም በሚል አላማ የሰዉን ህይወት ለመታደግ እየሰራ መሆኑን በመግለጽ ከበጎ ፍቃደኛ ለጋሾች በነጻ የሚቀበሉትን ደም ለምያስፈልጋቸዉ ሁሉ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

ደም ከለለ የሰዉን ህይወት ማስቀጠል የሚቻል ባለመሆኑ በየጊዜው የሚሰበሰበዉን ደም ለተለያዩ ስምንት ለሚሆኑ ሆስፒታሎች እንደሚሰጡ በመግለጽ ከእነዚህም መካከል የመቱ ካርል የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ፣ የበደሌ ሆስፒታል ፣ የቴፒ ሆስፒታል በዋናነት ተጠቃሽ ሲሆኑ በቅርቡ ወደ ስራ የገባው የማሻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልም ደም የሚያስፈልግ መሆኑን ነው የተናገሩት ።

በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለሚደርስባቸው ሰዎች እንድሁም በቀዶ ጥገና ወቅት የሰዉን ህይወት ለመታደግ ደም እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የደም ባንኩ በሸካ ዞን በማሻ እንድሁም በቴፒ በርካታ የደም ለጋሾች እንዳሉ በማንሳት በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ት/ት ቤት ተማሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የክረምት ጊዜ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በብዛት እንደሚለግሱ ገልጸዋል።

በዘንድሮው ዓመት ስድስት ሺህ ዩኒቲ ለመሰብሰብ ታቅዶ በእስካሁኑ ግማሽ ዓመት ብቻ የዕቅዱን መቶ ፔርሰንት ማሳካት መቻሉን ያነሱት ባለሙያው በባለፈው ዓመት ካሉት የደም ባንኮች ሁለተኛ መውጣቱን አብራርተዋል።

ከለጋሾች መካከል ከሶስት ጊዜ በላይ እንደለገሱ የሚናገሩት ወ/ሮ ሳራ ሳሙኤል እና አቶ እንዳልካቸው እንደሻው ህይወትን ለመተካት ሲሉ በደም እጦት ምክንያት ህይወታቸውን ለሚያጡ እናቶች እንድሁም በተለያዩ ምክንያቶች ደም ለሚያስፈልጋቸዉ ሁሉ በመለገስ ህይወታቸውን በመታደጋቸዉ ደስተኛ መሆናቸዉን ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጭዎቹ ደም በመለገሳቸዉ ምክንያት ምንም እንደማይሆኑም በመግለጽ ሁሉም ደም በመለገስ የሰዉ ህይወት እንዲታደግ ጠይቀዋል።