በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ያለው የዱባይ ማራቶን ዛሬ ሲከናወን በወንዶች አትሌት ቡቴ ገመቹ፤ በሴቶች ደግሞ አትሌት በዳቱ ሂርጳ አሸንፈዋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በማራቶን የሮጠው አትሌት ቡቴ ገመቹ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2፡04፡50 የሆነ ጊዜ ፈጅቶበታል፡፡
አትሌት ቡቴ የ80 ሺህ የአሜሪካን ዶላርም ተሸላሚ ሆኗል፡፡
አስቀድሞ በግማሽ ማራቶኖች ይሳተፍ የነበረው ቡቴ የዱባይ ማራቶንን በማሸነፉ መደሰቱን ተናግሯል፡፡
የመጀመሪያውን 36 ኪሎ ሜትር ከሮጥኩ በኋላ እንደማሸንፍ አቅሜን ተረዳሁት ሲልም ገልጿል ፡፡
ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከ1-10 ያለውን ደረጃ ይዘው በገቡበት የወንዶች ማራቶን አትሌት ብርሀኑ ጸጉ እና አትሌት ሽፈራ ታምሩ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡
በሴቶች በተደረገው ፉክክር አትሌት በዳቱ ሂርጳ በቀዳሚነት ፈጽማለች፡፡
አትሌቷ 2፡18፡27 በሆነ ሰዓት ርቀቱን በማጠናቀቅ የ80 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ሆናለች፡፡
ጠንክሬ በመዘጋጀቴ ለዚህ ክብር በቅቻለሁ ስትልም ተናግራለች፡፡
በሴቶች በተደረገው ውድድርም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከ1-10 ያለውን ደረጃ ሲይዙ፤ አትሌት ደራ ዲዳ እና አትሌት ትእግስት ግርማ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡
ለዚህ ውድድር ለኤሊት አትሌቶች የተዘጋጀውን 336 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማትንም ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ወስደውታል፡፡
More Stories
በኤፍ ኤ ካፕ 4ኛ ዙር ድልድል ሩበን አሞሪም ከሩድ ቫን ኔስትሮይ አገናኝቷል
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሠራተኞች መካከል የነበረው አለመግባባት በውይይት መፈታቱ ተገለጸ
በቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን አማን ከተማ ለቢስት ባር እሮጣለሁ በሚል መሪ ቃል የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሄደ