በእንስሳት ዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም ወደ ምርታማነት ለመቀየር ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ አሰራርን ማዘመንና ልዩ ትኩረት መስጠት ላይ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህም የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ትልቅ ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡
በሌማት ትሩፋት በልዩ ትኩረት ከሚሰሩ ስራዎች መካከል አንዱ የዶሮ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዶሮ እርባታ ምቹ የሆኑ ሥነ-ምህዳሮች ያሏት ሀገር ብትሆንም የዶሮ እርባታ ዘርፉ ለምግብ ስርዓቱ እና ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ሲያበረክት የነበረው አስተዋፅዖ ከተለያዩ መለኪያዎች አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ ሆኖ ቆይቷል።
ለዚህ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል ዋና ዋናዎቹ የሀገር ውስጥ የዶሮ ዝርያዎች ምርታማነት አነስተኛ መሆን እና ዝርያቸው የተሻሻሉ ዶሮዎች ከውጪ ለማስገባት የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት መኖር እንዲሁም የዶሮ መኖ ዋጋ ውድ መሆን ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የሌማት ትሩፋት የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያ አቅርቦትና ስርጭትን በመፍታት ምርታማነትን እያሳደገ ይገኛል፡፡
የተሻሻለ የዶሮ ዝርያ አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ኩባንያ ጋር በመተባበር የቅድመ ወላጅ ዶሮ ማዕከል (Grandparent stock farm) ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራችን እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ማዕከሉ በሌማት ትሩፋት የተያዙ ግቦችንና አጠቃላይ አገራዊ የዶሮ ልማትን ለማሳደግ ትልቁን ድርሻ እንደሚወጣ ይጠበቃል፡፡
በዚህ መነሻነት ማዕከሉ በሚቀጥሉት ወራቶች (ከሚያዝያ ወር ጀምሮ) በአጠቃላይ 550,000 የሚደርሱ ቴትራ ኤች የተባሉ የዶሮ ዝርያ ወላጅ ዶሮዎችን በማምረት ለማስፈልፈያ ተቋማት ያሰራጫል፡፡ የቴትራ ኤች የዶሮ ዝርያ ጥምር ጠቀሜታ ያላቸው (ለስጋና ለእንቁላል የሚሆኑ) ዶሮዎች ሲሆኑ ይህ ዝርያ በአሁኑ ሰዓት ከኢትዮጵያ ውጪ በአፍሪካ አህጉር በጋና፣ ሴኔጋል እና ቡርኪናፋሶ ይገኛል፡፡
እነዚህ ዶሮዎች በምርታማነታቸው የተመረጡ ሲሆን በአጭር ጊዜ እንቁላል የሚጥሉ፣ በሞት መጠናቸው አነስተኛ የሆኑ፣ የእንቁላል ምርታቸው በቤት ውስጥ እርባታ በአመት ከ230-250 የሚደርስ እና የእንቁላሉ ክብደትም የተሻለ ሲሆን ከ60-62 ግራም መጠን ያለው ነው፡፡
በመሆኑም ይህንን ማዕከል ውጤታማ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን በሀገር ውስጥ ያሉ የግልና የመንግስት ማስፈልፈያ ማዕከላትን ለማጠናከር፣ ጥራት ያለው የመኖ አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማስፋፋት እንዲሁም የዶሮ ስነ ህይወት ደህንነት ጥበቃ ስርዓትን ለመተግበር እና የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል፡፡
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።