ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ማዕድ ያጋሩት ከአዲስ አበባ ከተለያዩ ከፍለ ከተሞች ለተውጣጡ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ነው፡፡
የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩም በብሔራዊ ቤተመንግስት የተከናወነ ሲሆን፤ የአረጋውያኑና አካል ጉዳተኞች የብሔራዊ ቤተ-መንግስት ሙዚየምንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ከተገኙት መካከል ያነጋገራናቸው አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያከናወኑት በጎ ተግባር ልዩ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
አቶ ደበበ ጂዳ እና ወይዘሮ ከበደች ወርቁ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓሉን ከአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ጋር ማሳለፋቸው ሁሉም በየአካባቢው ሊተገብረው የሚገባ አርአያነት ያለው ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ አቶ ጌትነት ነጋሽ፤ እርስ በርስ መደጋገፍ የኢትዮጵያውያን መገለጫና እሴት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአቅመ ደካሞችና አረጋውያን በየጊዜው ማዕድ ከማጋራት በተጓዳኝ በልማት ስራዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለሚያከናውኑት ስራም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተለይ የልማት ስራዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ መንግስት እያከናወነ ያለውን ስራም አድንቀዋል፡፡
የብሔራዊ ቤተመንግስት ሙዚየምን ተዘዋውረው በመጎብኘታቸውም መደሰታቸውን አረጋውያኑ ተናግረዋል፡፡
አቶ ገብሩ ደስታ፤ ብሔራዊ ቤተ-መንግስት ሲገቡ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ጠቁመው፤ ሙዚየሙ የያዛቸው ታሪካዊ ቅርሶች አጠቃላይ ገጽታ እጅግ ማራኪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋውያን ብሔራዊ ቤተመንግስቱን እንዲጎበኙ በማድረጋቸውም አመስግነዋል፡፡
ውይዘሮ አስቴር ነጋሽ በበኩላቸው የብሔራዊ ቤተ-መንግስት ሙዚየም የተካተቱ ታሪካዊ ቅርሶች የኢትዮጵያን ገናናነት የሚያመላክቱ ስለመሆናቸው ገልጸዋል፡፡
እርስ በርስ በመደጋገፍና ሰላምን በመጠበቅ አሁንም ኢትዮጵያን ትልቅ ማድረግ እንደሚቻልም ነው የጠቆሙት፡፡
ደሬቴድ
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።