January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኃይል ማመንጫ ግድቦቹ በበጀት ዓመቱ የታቀደውን ኃይል ማግኘት የሚያስችል የውሃ መጠን መያዛቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የተቋሙ የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የዕቅድ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ጥሩወርቅ ሽፈራው እንደገለጹት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በሙሉ አቅማቸው ኃይል እንዲያመነጩ ግድቦች በቂ ውሃ መያዝ ይኖርባቸዋል።

በክረምቱ ወቅት ከፍተኛ የውሃ መጠን ያከማቹ ማመንጫ ጣቢያዎች ከፍተኛ ኃይል እንዲያመነጩ በማድረግ አነስተኛ ውሃ የነበራቸው ግድቦችን የኃይል ጭነት በመቀነስ በተገቢው መጠን ውሃ እንዲይዙ መደረጉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ግድቦች የያዙት የውሃ መጠን በበጀት ዓመቱ ለማመንጨት የታቀደውን ኃይል ማሳካት እንደሚያስችል ነው ያመላከቱት።

እንደ ስራ አስኪያጇ ገለፃ፤ ግልገል ጊቤ 1ኛ፣ ፊንጫ፣ መልካ ዋከና፣ ጣና በለስ፣ ተከዜ፣ ገናሌ ዳዋ፣ ቆቃ እና የህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ግድቦች የሞሉ ሲሆን ጊቤ 3ኛ እና አመርቲ ነሼ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ደግሞ በበቂ ደረጃ ውሃ ይዘዋል፡፡

ግድቦች የያዙትን የውሃ መጠን በአግባቡ ለመጠቀም ከጥገና፣ ከውሃ አስተዳደር እና ከመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት ጋር በተያያዘ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ወይዘሮ ጥሩወርቅ አመልክተዋል፡፡

የ2017 በጀት ዓመት የግድቦች የውሃ አያያዝ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የተሻለ እንደሆነ በዳሰሳ ጥናት መረጋገጡንም ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከተለያዩ የኃይል ምንጮች ከ25 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመለክታል