December 18, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

አሜሪካ እና ምዕራባውያን ሩሲያ ለከባድ አጸፋ እንድትነሳሳ እየገፋፏት ነው – ፕሬዚዳንት ፑቲን

ማሻ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2017 (ደሬቴድ ማሻ ቅርንጫፍ) አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሩሲያን ከልክ በላይ በመግፋት ለከባድ አጸፋ እንድትነሳሳ እየጎተጎቷት መሆኑን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስታወቁ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከሀገራቸው ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ጋር ባደረጉት ውይይት÷ አሜሪካ እና ምዕራባውያን ለዩክሬን የሚያደርጉት ወታደራዊ ድጋፍ ሩሲያ ለከባድ አፀፋ እንድትዘጋጅ እየገፋፋት ነው ብለዋል፡፡

ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ዘርፈ-ብዙ ጦርነት አውጀዋል፤ ይህም የሩሲያን ቀይ መስመር ያለፈ በመሆኑ ሞስኮ የደኅንነት ስጋት ውስጥ እንድትገባ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

በተለይም አሜሪካ ሩሲያን ለማዳከም እና በጦርነቱም እንድትሸነፍ ለዩክሬን ገንዘብን ጨምሮ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያደረገች ነው ማለታቸውን አርቲ ዘግቧል፡፡

አሜሪካ ሩሲያን ለማጥቃት የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤሎችን በፖላንድ ድንበር ማሰማራቷን ጠቅሰው÷ የሩሲያን የበላይነት ለማዳከምም ቅጥረኛ ወታደሮችን እና የጦር አማካሪዎችን መላኳን ገልጸዋል፡፡

ዋሽንግተን ሶቭየት ሕብረትን ለማፍረስ የተጠቀመችበትን ታክቲክ አሁንም እየደገመችው ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ ሞስኮ የአሜሪካን እንቅስቃሴ በዝምታ እንደማታልፈው እና ከባድ አፀፋዎችን ልትሰጥ እንደምትችል ጠቁመዋል፡፡

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር አንደሬይ ቢሎዞቭ አሜሪካ በፖላንድ እና ከሩሲያ በ165 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኙት የጦር ሰፈሮቿ ቶምሃውክ የተሰኙ ክሩዝ ሚሳኤሎችን ልታስወንጭፍ እንደምትችል አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም አሜሪካ በስምንት ደቂቃዎች ሞስኮን መምታት የሚችል የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤል በጀርመን በኩል ልታሰማራ እንደምትችል ገልጸው÷ ለዚህም ሩሲያ በአካባቢው ጠንካራ የአየር መከላከያ ሥርዓት መገንባት እንደሚጠበቅባት በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን÷ ከሰሞኑም ዩክሬን በታጋኖርግ ግዛት ለፈፀመችው የሚሳኤል ጥቃት ሩሲያ በዩክሬን ኢነርጅ መሠረተ-ልማቶች ላይ የአፀፋ ጥቃት መፈፀሟ ይታወሳል፡፡