November 7, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ለ5 ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የሥራ ፈቃድ ተሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለአምስት ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የሥራ ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ፡፡ባንኩ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትና ተደራሽነትን ለማስፋፋትና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማዳበር አሁን በሥራ ላይ ካሉት ከባንክ ጋር ከተያያዙ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በተጨማሪ ከባንክ ጋር ዝምድና የሌላቸው የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችን ለመክፈት የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ መመሪያ ማውጣቱን አስታውሷል፡፡በዚሁ መሠረት ተፈላጊውን መስፈርት ማሟላታቸው ተረጋግጦ በመመሪያው ንኡስ አንቀጽ 4.2 መሠረት እንዲንቀሳቀሱ ለዱግዳ ፊደሊቲ ኢንቨስትመንት ፒኤልሲ፣ ኢትዮ ኢንዲፔንደንት ፎሬይን ኤክስቼንጅ ቢሮ፣ ግሎባል ኢንዲፔንደንት ፎሬይን ኤክስቼንጅ ቢሮ፣ ሮበስት ኢንዲፔንደንት ፎሬይን ኤክስቼንጅ ቢሮ እና ዮጋ ፎሬክስ ቢሮ ፈቃድ መሰጠቱን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በሙሉ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ሀገር ጥሬ ገንዘቦችን በመግዛትና በመሸጥ እንዲሁም ከባንኮች ጋር በመቀናጀት ለወጪና ገቢ ንግድ የሚውል የውጭ ምንዛሪ በማመቻቸት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገበያ ለማስፋፋትና ለማዳበር የሚረዳ ሚና ይኖራቸዋል ብሏል ባንኩ፡፡የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በዋናነት የሚያካሂዱት የውጭ ምንዛሪ ሽያጭም ሆነ ግዥ ወዲያውኑ የሚፈጸም ብቻ እንደሚሆንም ነው ብሔራዊ ባንክ ያስታወቀው፡፡የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ያለ ጉምሩክ ዴክላራሲዮን ከደንበኞች እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር፣ የጉምሩክ ፈቃድ ከሚያቀርቡት ደግሞ ከዚያ በላይ የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ መግዛት እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡እንዲሁም ተፈላጊ የጉዞ መረጃ ላላቸው የግል ተጓዦች እስከ 5 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ ለንግድ ሥራ ተጓዦች ደግሞ እስከ 10 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በጥሬ ገንዘብ መሸጥ ይችላሉ ነው የተባለው፡፡የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጡ የአሠራር፣ የደህንነት፣ የሪፖርት አደራረግና የመዝገብ አያያዝ መስፈርቶችን በአግባቡ ተግባራዊ ስለማድረጋቸው ባንኩ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያደርግም በአጽንኦት ገልጿል፡፡