January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኢትዮጵያን በተለያዩ ዘርፎች እንደሚያግዝ አስታወቀ

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኢትዮጵያ በሕክምና፣ ትምህርት፣ ግብርና እና ሌሎች ዘርፎች የምታከናውናቸውን ተግባራት እንደሚያግዝ አስታወቀ፡፡ኢትዮጵያ በኦስትሪያ-ቪየና በተካሄደው 68ኛው የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢንርጂ ኤጀንሲ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ተሳትፋለች፡፡የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር ከዚህ በፊት ከኤጀንሲው ጋር በትብብር የተሠሩ ሥራዎችን ጠቅሰው÷ በቀጣይም ኤጀንሲው በሚያከናውናቸው ዋና ዋና የቴክኒክ ትብብሮች ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን ጠይቀዋል፡፡ሰላማዊ የኒውክሌር ሣይንስና ቴክኖሎጂ ልማትን በማጎልበት በተለይም በጤና፣ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግና ኃይል ልማት ዘርፎች የበለጠ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት ኤጀንሲው አጠናክሮ እንዲደግፍ ጠይቀዋል።68ኛው ጉባዔም በግብርና ምርታማነት ላይ ትኩረት የሚያደርግ “Atoms4Food” የተሰኘ አዲስ ኢኒሼቲቭ ይፋ ማድረጉን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡ኢኒሼቲቩ የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ተግዳሮት ያለባቸው ቀጣናዎችና ሀገራት የኒውክሌር ሣይንስና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርና ምርምርና ምርትን ለማሳደግ ያግዛል ተብሏል፡፡ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት አብራርተው÷ ኤጀንሲው ይፋ ባደረጋቸው ኢኒሼቲቮች በቀጣይ ቀዳሚ ተጠቃሚ እንድትሆን በአጽንኦት ጠይቀዋል።ሚኒስትሩ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ማሪያኖ ግሮሲ ጋር ተወያይተዋል።በውይይታቸውም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር በኢትዮጵያ የካንሰር ሕክምና ማዕከላትን አቅም ማሳደግና ተጨማሪ ማዕከላትን ለማስፋፋት፣ የቆላ ዝንብ ማጥፊያ ፕሮጀክት ማዕከልን ለማጠናከር፣ የኒውክሌር ኢንጂኔሪንግ ፕሮግራም የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎችን በተለየ ሁኔታ እንደሚያግዙ ገልጸዋል።በተጨማሪም በጉባዔው ይፋ በተደረገው “Atoms4Food” መርሐ-ግብር መሠረት ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት በቀጣይ ለመደገፍ እንደሚሰሩ ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።