October 4, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በአዲስ አበባ ለብዙሀን ትራንስፖርት ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ 14 መስመሮች ይፋ ሆኑ

አገልግሎቱ በተመረጡት መስመሮች ላይ ከመጪው እሁድ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል የአዲስ አበባ ትራስፖርት ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ ለብዙሀን ትራንስፖርት ብቻ አገልግሎት ይሰጣሉ የተባሉ 14 መስመሮችን ይፋ አድርጓል፡፡ ቢሮው ይፋ ባደረገው መግለጫ ከትምህርት መከፈት ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን መጨናነቅ ለማስቅረት ውሳኔው አስፈላጊ ነው ብሏል። ቢሮው የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ የብዙሀን ትራንስፖርት አማራጮችን መጠቀም ብዛት ያለው ሰው በአንድ ጊዜ እንዲመላለስ በማድረግ እና የመንገድ መዘጋጋትን ለመቀነስ እንደሚረዳ ገልጿል፡፡በዚህም ከመጪው እሁድ መስከረም 12 ጀምሮ የብዙሀን ትራንስፖርት የሚባሉት ከ8 ሰው በላይ የሚጭኑ ተሸከርካሪዎች ብቻ ይጓዙባቸዋል የተባሉ 14 መስመሮችን ቢሮው ይፋ አድርጓል፡፡ እነርሱም ከቦሌ- ፒያሳ፣ ከቦሌ- ሜክሲኮ፣ ከቦሌ- አራት ኪሎ፣ ከቦሌ- አውቶቢስ ተራ፣ ከቦሌ- ሽሮሜዳ፣ ከጀሞ- ፒያሳ እና ከጀሞ- ሜክሲኮ ናቸው፡፡በተመሳሳይ ከፒያሳ- ቦሌ፣ ከሜክሲኮ- ቦሌ፣ ከአራት ኪሎ- ቦሌ፣ ከአውቶቡስ ተራ- ቦሌ፣ ከሽሮ ሜዳ- ቦሌ፣ ከፒያሳ ጀሞ እና ከሜክሲኮ – ጀሞ የሚገኙ መስመሮች የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ መሰጠት እንደሚጀምሩ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡አዲስ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው አሰራር ከተማሪና መምህራን ባለፈ ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች በሰዓታቸው ወደ ሚፈልጉት ቦታ በመንቀሳቀስ አገልግሎት እንዲያገኙ ያግዛል ተብሏል፡፡ተገልጋዮች የሚያጋጥሟቸውንና የሚስተዋሉ ችግሮችን በአቅራቢያ ለሚገኙ የትራንስፖርት ቁጥጥር ሰራተኞች ወይም በ 9417 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጡ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል፡፡

Al-Ain