ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የሚያቋቁሙት የኮሪደር አስተዳደር የወደብና የትራንስፖርት አገልግሎት ቀልጣፋ እንዲሆን ያስችላል ተባለ፡፡የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ በጅቡቲ ወደብ ላይ የአሰራር አለመቀላጠፍ ከገጠመ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትና ተወዳዳሪነት ላይ ትልቅ ተጽእኖ ይኖረዋል።ወደ ሀገር የሚገቡና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በጅቡቲ ወደብ በኩል እንደሚተላለፉ ጠቅሰው፤ የወደብ አገልግሎቱ ቀልጣፋ ካልሆነ ምርቶች በውጭ ገበያ የመወዳደር ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡የወጪ እና ገቢ ንግዱን እንዲሁም በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መካከል የሚካሄደውን ንግድ በተቀላጠፈና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማካሄድ የጋራ የኮሪደር አስተዳደር ለማቋቋም ስምምነት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ቀሪ ስራዎች ታይተው አዲስ አበባ ላይ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ስብሰባ በማድረገ የጋራ የኮሪደር አስተዳደር ጉዳይን ለመጨረስ ተስማምተናል ነው ያሉት፡፡የጅቡቲ የንግድና ቱሪዝም ሚኒስትር አሊ ዳውድ አብዱ በበኩላቸው÷ ከሁለት አመት በፊት የኮሪደር አስተዳደር ባለስልጣን ለማቋቋም በሀገራቱ መካከል የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል ብለዋል፡፡የስምምነቱ አላማ የሚያስፈልገውን የቴክኒክ፣ የሰው ሃይልና ፋይናንስ እንዲሁም የወደፊት የባለስልጣኑን ዋና መቀመጫን የሚወስን ኮሚቴ ለማቋቋም መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡የጋራ የኮሪደር አስተዳደር ባለስልጣን መቋቋሙ በተለያየ መልኩ የሚሰሩ ስራዎችን ሀገራቱን ወክሎ በመስራት የወደብ፣ የትራንስፖርትና አጠቃላይ አገልግሎቱን ቀልጣፋ እንዲሆን ያደርጋልም ተብሏል፡፡ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በሎጂስቲክ፣ በንግድና በሌሎች አገልግሎቶች ላይ የሚገጥሟቸውን ችግሮች የሚፈቱበት የሁለትዮሽ ኮሚሽን እንዳላቸው ጠቅሰው፤ አዲስ የሚቋቋመውን የጋራ የኮሪደር አስተዳደር ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችሉ ውይይቶች እየተደረጉ እንደሆነ ጠቁመዋል።
FBC
More Stories
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከፑቲን ጋር የሚያደርጉት ንግግር እየተመቻቸ መሆኑን ገለጹ።
የአሜሪካ ኮንግረስ በአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ድምጽ ሰጠ
አስደንጋጩ የሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳት አልበረደም